
በአዲሱ የመንግሥት ምሥረታ ዙሪያ አስተያየታቸውን የሰጡ የደብረ ማርቆስ ከተማ ወጣቶች መንግሥት በምርጫ ወቅት የገባውን ቃል በተግባር በመተርጎም የሰላም፣ የልማት እና የሥራ ዕድል ፈጠራ ጥያቄዎችን እንዲመልስ እንሻለን ብለዋል። ወጣቶቹ የሰላም መረጋገጥ እና ሀገራዊ አንድነት ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው ጉዳይ መኾኑንም ነው ያነሱት።
አዲሱ መንግሥት በሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች መካከል እኩልነትን፣ ፍትሕን እና የጸናች ኢትዮጵያን የሚፈጥር አሠራር እንደሚዘረጋም ተስፋ እንዳላቸው ገልጸዋል። በቀበሌም ኾነ በክልል ደረጃ የተጀመሩ የልማት ሥራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ እና ሕዝቡን በተጨባጭ ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሥራዎች እንዲከናወኑ እንሻለንም ነው ያሉት።
የወጣቶች የሥራ አጥነት ችግርን ለመፍታት የሙያ ሥልጠናዎችን እና የሥራ ዕድሎችን ማስፋት ይገባልም ብለዋል። ዜጎች በየትኛውም የሀገሪቱ ክፍል ተንቀሳቅሰው የመሥራት መብታቸው ሊረጋገጥ እንደሚገባም አሳስበዋል። የሴቶች እና የወጣቶች ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባም ገልጸዋል።
ዜጎች ከተረጅነት ተላቅቀው በምግብ ራሳቸውን እንዲችሉ እና በየደረጃው ያለው የመንግሥት መዋቅር ሕዝብን በታማኝነት እና በቅንነት እንዲያገለግልም ጠይቀዋል።
ወጣቶቹ አዲስ ለሚመሠረተው መንግሥት እና መሪዎች ዕምነት እንዳላቸው እና የገቡትን ቃል ለማስፈጸም በሚያደርጉት ጥረት ከጎናቸው እንደሚቆሙም ገልጸዋል።
መንግሥትም በተባበረ ክንድ የተጣለበትን ሀገራዊ ኀላፊነት እንዲወጣ እንደሚሹ ጠቁመዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
