#ትልቅ ሀገር፣ ትልቅ ሕዝብ፣ ታላቅ ርዕይ!

25
በችግሮች እንደወርቅ ተፈትኖ እየበረታ የቀጠለው የአማራ ክልል የአመራርነት ጥበብ።  የአማራ ሕዝብ በሀገረ መንግሥት ግንባታ ታሪክ ውስጥ ደማቅ አሻራ፣ ለመንግሥት መጽናት እና ሕግ የበላይነት መከበር ጽኑ አቋም ያለው ሕዝብ ነው።
በተለያየ ወቅት ተቀያያሪ እና ተለዋዋጭ መልክ እየያዘ የዘለቀው ሀገር አቀፍ የፖለቲካ ሁነት ሳይበግረው ውስጣዊ አንድነቱን አጠናክሮ በሀገረ መንግሥት መጽናት የሚጠበቅበትን ድርሻም ሲወጣ የኖረ ሕዝብ ነው።
ከሕዝቡ የወጡት መሪዎችም እንደ ማዕበል የሚናወጥ እና ተቀያያሪ የፖለቲካ ዑደት በሚስተዋልበት ክልላዊ፣ ሀገራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ሁኔታዎች አውድ ውስጥ ይኾናል የሚሉትን አመራርነት እየሰጡ ከዚህ ትውልድ ላይ ደርሰዋል።
በተለይም ባለፉት ዓመታት ክልሉ ችግር ባጋጠመው ወቅት የክልሉን መንግሥት በማጽናት፣ በቁርጠኝነት እና መስዋትነትን በመክፈል ጭምር ክልሉ ከተጋረጠበት አደጋ ማውጣት ችለዋል። የሰላም ሁኔታውም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መጥቷል።
በችግር ወቅት የመጣው የክልሉ መንግሥት አመራር ከችግሮች ጋር ተጋፍጧል። ክልሉ ከተፈጠረው የጸጥታ ችግር እንዲወጣ ሰፊ የሕዝብ ውይይቶችን በማድረግ የሰላም ሁኔታን መመለስ ተችሏል።
የተጀመሩ የልማት ሥራዎችንም በተሻለ ግለት እንዲቀጥሉ አስችሏል። በበርካታ ከተሞች የልማት ብርሃን እንዲፈነጥቅ ማድረግ የቻለ የአመራር ቁርጠኝነትም ታይቶበታል።
የክልሉ መንግሥት የጦርነት እና የግጭት እሳትን እያጠፋ ለልማት ሥራዎች ልዩ ትኩረት ሰጥቷል። የተመዘገቡት የልማት እና የሰላም ግንባታ ሥራዎች በክልሉ ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ የሚመራው የክልሉ መንግሥት ዋና የጥንካሬ ማሳያዎች ተደርገው የሚወሰዱ ናቸው።
ለዚህም የክልሉ ምክር ቤት ለርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ዕውቅና ሰጥቷቸዋል። ለአመራር ብቃታቸውም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል። የአማራ ክልል ሕዝብ በራሱ አቅም በተሟላ መንገድ ማሥተዳደር የቻለበት ወቅት እንደነበርም ጠቁመዋል።
ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደን “ከነ ሙሉ ክብራቸው እና ከተሰጣቸው ሥልጣን ጋር የሚወስኑ፣ የተከበሩ፣ የተወደዱ፣ የታመኑ፣ ሠርተው የሚያሠሩ መሪ ናቸው” በማለትም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለርእሰ መሥተዳድሩ መስክርነታቸውን ሰጥተዋል።
ይህ የተደመረ የአመራርነት ጥንካሬ ውጤትም ችግሮችን በብቃት ተወጥቶ የሕዝቡ ታሪክ አንዱ አካል የኾነውን የመንግሥት ምሥረታ በዛሬው ዕለት አካሂዷል።
በአሰፋ ልጥገበው
‎የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleትልቅ ሀገር፤ ትልቅ ሕዝብ፤ ታላቅ ርዕይ
Next article#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ! ከአዲሱ የክልሉ መንግሥት ምሥረታ ወጣቶች ምን ይሻሉ?