🌾 በአዴት ግብርና ምርምር ማዕከል የተመዘገቡ ስኬቶች እና የለውጥ ጉዞ!

1

 

የአዴት ግብርና ምርምር ማዕከል ከ1978 ዓ.ም ጀምሮ በኢትዮጵያ የግብርና ታሪክ ውስጥ አሻራውን ያሳረፈ በሳይንስ እና በቴክኖሎጂ የታገዘ ምርምር በማድረግ አስተዋጽኦ ሲያደርግ የቆየ ታላቅ ተቋም ነው።

ማዕከሉ ከክልል፣ ከወረዳ እና ከቀበሌ ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ለማድረግ ሰፊ ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝም የማዕከሉ ዳይሬክተር ምሥጋናው ፈረደ ነግረውናል።

🚀 አዳዲስ እና ምርጥ የሰብል ዝርያዎች ማቅረብ፣ የአፈር ለምት እና የምርምር ሥራዎች፣ የደን ምርምር፣ ቅንጅታዊ አሠራር እና የቴክኖሎጂ ስርጸት በማዕከሉ የተከናወኑና ውጤቶች የተገኙባቸው ዋና ዋና ሥራዎች መኾናቸውንም ገልጸዋል። የበቆሎ እና ስንዴ ዋና ዋና ዝርያዎችን በዝናብ እና በመስኖ በማልማት ለምርጥ ዘር ማኅበር ድርጅቶች እና ለአርሶ አደሮች መነሻ ዘር እያቀረበ ይገኛልም ብለዋል።

የተለያዩ ዓይነት የጤፍ ዝርያዎች (ቁንጮ፣ ጽዮን፣ ጸደይ እና ኅብር የተባሉ የጤፍ ዝርያዎች) የአርሶ አደሮችን ፍላጎት መሠረት በማድረግ ተደራሽ ኾነዋል ነው ያሉት። አርሶ አደሮች አጠውልግ በመባል የሚታወቀው የድንች በሽታ እያስቸገራቸው ከመኾኑ ጋር ተያይዞ ከሌሎች ተቋሞች ጋር በመተባበር በሽታውን የመከላከል፣ ድንችን ለዘር አባዥ ማኅበራት፣ ለምርጥ ዘር ድርጅቶች እና ለአርሶ አደሮች በስፋት እንዲሰራጭ ማድረጉንም ገልጸዋል። በሀገር አቀፍ ደረጃ የድንች ዘር ምርምርን የሚያስተባብረው የአዴት ግብርና ምርምር ማዕከል መኾኑንም ጠቅሰዋል።

ከአፈር ለምነት እና ምርምር ሥራዎች አኳያም የሀገሪቱን የግብርና ፍላጎት መሠረት በማድረግ የማዳበሪያ (ዳፕ እና ዩሪያ) አጠቃቀምን በምርምር በማረጋገጥ ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ በማድረግ ረገድ ከፍተኛ የመረጃ ድጋፍ ተሰጥቷልም ነው ያሉት።

የተፈጥሮ ማዳበሪያ እና የአሲዳማ አፈር አሥተዳደር ላይም በርሚ ኮምፖስት እና ኖራን ከኮምፖስት ጋር በስፋት በመጠቀም ከምርት ውጪ ኾኖ የነበረን መሬት መልሶ ወደ ማምረት አቅም መመለስ እንደተቻለም አንስተዋል። በተለይም ለስንዴ ሰብል ጥቅም ላይ እንደዋለም አመላክተዋል። የደን ምርምር ላይም ሰፊ ሥራዎች መሠራታቸውን ጠቅሰዋል።

ሌላው ማዕከሉ ትኩረት አድርጎ የሠራበት እና ቀጣይም የሚሠራበት ቅንጅታዊ አሠራር እና የቴክኖሎጂ ስርጸት መኾኑን የተናገሩት ዳይሬክተሩ ከክልል ግብርና ቢሮ ጋር በመተባበር የአርሶ አደሮችን ፍላጎት ቀድሞ በመሠብሠብ እንደሚሠራ ተናግረዋል። የምርምር ውጤቶችን በፓኬጅ በማዘጋጀት እና በሥልጠና ጭምር በማገዝ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሥራዎች እየተሠሩ እንደኾነም ገልጸዋል። ይህም በቀጣይ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

🌟 የአዴት ግብርና ምርምር ማዕከል በአየር ንብረት መዛባት እና በሌሎች ተግዳሮቶቸ ሳይበገር የምርት እና የምርት ጥራት ማነስ ችግርን ለመቅረፍ በሳይንስ እና በምርምር የታገዘ አሠራርን በመዘርጋት የነገዋን የበለጸገች ኢትዮጵያ በጽኑ መሠረት ላይ እያነጸ ይገኛል ነው ያሉት።

#የመደመር_መንግሥት!

#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ! 🇪🇹

#የአዴት_ግብርና_ምርምር_ማዕከል #አማራክልል_ምርምር_እና_ልማት

#ባሕር_ዳር #ጥቅምት_21_2019_ዓ_ም

✍️ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleየክልሉን የግብርና ዕድገት የሚያፋጥኑ ውጤታማ የምርምር ሥራዎች እየተሠሩ ነው።
Next articleአዲስ አበባ የ2026 የከተሞች ዘላቂ ልማት ዓለም አቀፍ ሽልማት ተሸለመች።