
የአማራ ክልልን የተፈጥሮ ሀብት ወደ ላቀ የኢኮኖሚ ውጤት በመቀየር የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በተያዘው ግብ የግብርናውን ዘርፍ በቴክኖሎጂ እና በምርምር ለመደገፍ ሰፊ እንቅስቃሴ እየተደረገ ይገኛል።
በአማራ ክልል ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የቴክኖሎጂ ብዜት እና ዘር ምርምር ዳይሬክተር አዕምሮ በዛብህ(ዶ.ር) እንደተናገሩት የክልሉን የግብርና ዕድገት የሚያፋጥኑ ውጤታማ የምርምር ሥራዎች እየተሠሩ ነው።
ኢንስቲትዩቱ የክልሉን የግብርና ልማት ዕቅድ ለማሳካት የሚያስችሉ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በምርምር ማምጣት፣ የወጣን ቴክኖሎጂ ለተጠቃሚዎች ማስተዋወቅ እና መነሻ ዘር ማቅረብ ዓላማ አድርጎ እየተሠራ ነው ብለዋል።
በዚህም የተጠቃሚዎችን ፍላጎት እና በክልሉ የሰብል ልማት ፍላጎት መሠረት ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያስችሉ ውጤታማ ሥራዎችን እየሠራ ይገኛል ነው ያሉት።
ለአብነትም በመደበኛ ሰብሎች በበቆሎ፣ በስንዴ፣ በማሽላ፣ በጤፍ፣ በአኩሪ አተር እና በመሳሰሉት ሰብሎች ላይ ተጨባጭ ለውጦች መምጣታቸውን ገልጸዋል። በንጥረ ነገር ምግቦችም በቦለቄ፣ በአተር፣ በባቄላ እና በሽንብራ ጥሩ ውጤቶች መምጣታቸውን አብራርተዋል።
በነባር የምርጥ ዝርያዎች ላይ የፍላጎት ችግር የለም ያሉት ዳይሬክተሩ አባዥ ተቋማት አዳዲስ ዝርያዎችን የመፈለግ ውስንነቶች እንደሚስተዋልም ጠቁመዋል።
ችግሩን ለመቅረፍም በምርምር የሚወጡት አዳዲስ ዝርያዎች ለተጠቃሚዎች እንዲደርሱ ከግብርና ቢሮ እና ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመተባበር እስከ ታች ድረስ ወርዶ የማስተዋወቅ ሥራ እንደሚሠራም አንስተዋል።
በመደበኛ ሰብሎች ላይ ባለፉት ዓመታት በሽፋንም በመጠንም፣ በጥራትም እየተሻሻለ መምጣቱን አንስተዋል። በኢንዱስትሪ እና ለውጭ ገበያ በሚቀርቡ ሰብሎች ላይም ፍላጎቱን ለማሳደግ ከተለያዩ ተቋማት ጋር በትብብር እየተሠራ መኾኑንም ተናግረዋል።
በቀጣይም አሁን የተጀመረውን ጥረት በማጠናከር በኢንዱስትሪ እና ለውጭ ገበያ በሚቀርቡ ሰብሎች ላይ ከአባዥ ተቋማት ጋር በትብብር የመሥራት ሂደቱ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመላክተዋል።
ለግብርናው ዕድገት የመነሻ ምርጥ ዘር ማዳረስ ወሳኝ ነው ያሉት ዳይሬክተሩ ሁሉም የሚመለከታቸው ተቋማት የማስተዋወቅ፣ ፍላጎት የመፍጠር እና የማዳረስ ሥራውን በቅንጅት መሥራት እንደሚገባቸውም አስገንዝበዋል። ለዘር አባዥ ተቋማትም አስፈላጊው ድጋፍ ሊደረግ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
#የመደመር_መንግሥት!
#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ! 🇪🇹
#ባሕር_ዳር #ጥቅምት_21_2019_ዓ_ም
✍️ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
