
”አዲሱ ምክር ቤት የሕዝብ ተስፋ እና አደራ ወደ ተግባር የሚቀየርበት ነው” አፈጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ የአማራ ብሔራዊ ክልል ምክር ቤት ሰባተኛ ዙር አንደኛ ዓመት የሥራ ዘመን መሥራች ጉባኤውን እያካሄደ ነው።
በጉባኤው መክፈቻ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የምክር ቤቱ ዋና አፈጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ስኬታማ እንደነበር ገልጸዋል። ድህረ ምርጫውም ሰላማዊ እና ስኬታማ ነው ያሉት አፈጉባኤዋ ምርጫውን ለማደናቀፍ የሞከሩ ኀይሎችን አንገት ያስደፋ ምርጫ እንደነበር ተናግረዋል።
የክልሉ ሕዝብ ሀገረ መንግሥትን ለማጽናት ጥይት እየተተኮሰበት ወኪሎቹን መምረጡን ገልጸዋል። አሁን ላይ አደራውን ለተመራጮች መስጠቱንም ተናግረዋል። ምርጫው ለሌሎች ሀገራትም ተሞክሮ የሚወሰድበት እንደኾነ አንስተዋል።
ለመረጠን ሕዝብ ታማኝነታችንን እና አክብሮታችንን መግለጽ አለብንም ነው ያሉት። አዲሱ ምክር ቤት የሕዝብ ተስፋ እና አደራ ወደ ተግባር የሚቀየርበት መኾን እንዳለበት ገልጸዋል።
የምክር ቤት አባላት በኀላፊነት እና በተጠያቂነት መምረጥ እንዳለባቸውም ተናግረዋል። የራስን ፍላጎት እና ጥቅም ወደ ጎን በመተው የሕዝብ ጥቅምን ማስከበር ላይ ቅድሚያ መስጠት ያስፈልጋል ብለዋል።
በአዲሱ ምክር ቤት ዘጠኝ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች 16 መቀመጫዎችን ማግኘታቸውንም አንስተዋል። ምክር ቤቱ ብዝኀነት የሚታይበት ነው ያሉት ዋና አፈጉባኤዋ ይሄን ዕድል በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባም ተናግረዋል።
ባለፉት ዓመታት የታዩ ጥንካሬዎችን ማስቀጠል፣ ደክመቶችን በማረም ለሕዝብ ተጠቃሚነት መሥራት እንደሚገባም አስገንዝበዋል። አዲሱ ምክር ቤት የሕዝብ አመኔታን መገንባት እንዳለበትም አንስተዋል።
አዲሱ ምክር ቤት ተስፋ ወደ ተግባር የሚቀየርበት መኾኑን እንዳለበት ገልጸዋል።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
