ትልቅ ሀገር፣ ትልቅ ሕዝብ፣ ታላቅ ርዕይ!

18
ሰላማዊ የምርጫ ተሳትፎ እና አዲስ የመንግሥት ምሥረታ፤ ለትልቅ ሀገር፣ ለትልቅ ሕዝብ እና ታላቅ ርዕይ ወሳኙ ምዕራፍ!
የአማራ ሕዝብ በኢትዮጵያ የታሪክ አጋጣሚዎች ሁሉ የመንግሥት ምሥረታ እና የሀገር ግንባታ ምሰሶ ኾኖ የዘለቀ ታላቅ ሕዝብ ነው ይላሉ በጂንካ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ ምሁሩ ምስክር ከተማ።
ኢትዮጵያ ባለፉት ሰባት ሀገራዊ ምርጫዎች ባካሄደችበት የዴሞክራሲ ልምምድ ውስጥ የአማራ ሕዝብ እንደ ሌሎች የሀገሪቱ ሕዝቦች ሁሉ ምርጫን በሰላማዊ መንገድ የመምራት እና የመሳተፍ ከፍተኛ የሥነ-መንግሥት ባሕል እና ጠንካራ አቋም እንዳለው በተግባር ሲያሳይ ቆይቷል ነው ያሉት።
መምህር ምስክር ከተማ ለአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ እንደተናገሩት በተለይም ባለፉት ሦሥት ዓመታት በአካባቢው የነበረው የሰላም እጦት በምርጫው ሂደት ላይ እንቅፋት ሊፈጥር ይችላል የሚሉ ሥጋቶች ቢኖሩም ሕዝቡ የሰላማዊ ሥልጣን ሽግግር እና የምርጫን ወሳኝነት በጥልቀት በመገንዘብ ችግሮችን ተጋፍጦ ይኾነኛል ያለውን አማራጭ በነጻነት እንደመረጠም አስረድተዋል።
በዚህ ሂደት ውስጥ ገዥው ፓርቲ እና ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምርጫው ሰላማዊ እና ስኬታማ እንዲኾን በትዕግሥት እና በተግባቦት የሠሩበት መንገድ ለወደፊቱ ትውልድ የሚማርበት ታሪካዊ አደራ ኾኖ አልፏል ብለዋል።
ሕዝቡም የተፎካካሪዎችን ሰላማዊ የምርጫ እንቅስቃሴ እና የቀረቡትን ለሕዝብ የሚጠቅሙ ፕሮግራሞች በሚገባ መዝኖ ድምጹን መስጠቱን መመልከታቸውን ጠቁመዋል።
አሁን ላይም የፌዴራል ሥርዓቱ በሚደነግገው መሠረት፣ ማዕከላዊው መንግሥት ከመመሥረቱ በፊት የፌዴራሉን መንግሥት የሚያዋቅሩት አባል ክልሎች ክልላዊ መንግሥታቸውን በማዋቀር ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
በዚህም መሠረት የክልሉ ሕዝብ በአብላጫ ድምጽ የመረጠው ፓርቲ ለሕዝብ የገባውን ቃል ሊፈጽም የሚያስችለውን አዲስ የመንግሥት አወቃቀር ምሥረታ ዛሬ ያካሂዳል ብለዋል።
ይህ አዲስ የመንግሥት ምሥረታ በክልሉ ፈጣን ልማትን ለማረጋገጥ፣ የሕግ የበላይነትን ለማስከበር እንዲሁም የሀገርን ሉዓላዊነት በማስጠበቅ ረገድ ከሕዝቡ ጋር በአንድ መስመር የሚራመድ ጠንካራ አና ብቁ የመንግሥት አካል ለመፍጠር ትልቅ አቅም እንደሚኾን ይጠበቃል ነው ያሉት።
ከዚህ የመንግሥት አካል ብዙ እንደሚጠበቅም አንስተዋል።
በምሥጋናው ብርሃኔ
‎የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous article“የአፍሪካን የወደፊት እጣ ፈንታ በጋራ ልንገነባው የተገባ ኃላፊነታችን ነው” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)
Next article#ትልቅ ሀገር፣ ትልቅ ሕዝብ፣ ታላቅ ርዕይ!