
ለትልቅ ሀገር፣ ለትልቅ ሕዝብ እና ለታላቅ ርዕይ ዘመናዊ ወታደራዊ ቁመና ያለው ሠራዊት። ኢትዮጵያ ሀገራዊ ሉአላዊነቷን፣ የሕዝቦቿን ሰላም እና ደኅንነት ማስከበር የሚችል ዘመኑ የደረሰበትን የጦር ቴክኖሎጂ የታጠቀ የምድር፣ የአየር እና የየብስ የበላይነቱን ያረጋገጠ አስተማማኝ የጸጥታ ተቋም በመገንባት ላይ ትገኛለች።
«ምድሩም ሰማዩም የብሱም የእኛ ነው!» በሚል ቁርጠኝነት የተገነባው የሀገር መከላከያ ሠራዊት የአየር የየብስ እና የባሕር ኀይልን ባቀናጀ መልኩ የምሥራቅ አፍሪካ የሰላም እና የጸጥታ አለኝታነቱን በተግባር እያስመሰከረ ይገኛል።
የኢፌዴሪ ጦር ኀይሎች ጠቅላይ አዛዥ እና የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) የጦር ኀይሉ የሪፎርም እና ዘመናዊነት ጉዞ ሀገርን የማስከበር ዋስትናን ብቻ ሳይኾን የቀጣናውን ሰላም ዘላቂ የሚያደርግ አቅም መገንባቱን አረጋግጠዋል።
«ሀገራዊ ሉአላዊነታችንን የሚደፍር ማንኛውንም ኀይል ለመመከት የሚያስችል አቅም ገንብተናል፤ ሰማያችንም ኾነ ምድራችን ሙሉ በሙሉ በቁጥጥራችን ስር ናቸው፤ የሠራዊታችን ቁመናም የኢትዮጵያን ታላቅነት እና ጽናት የሚያንጸባርቅ ነው» በማለትም የጸጥታ ኀይሉን ዘመናዊ ወታደራዊ ቁመና አንጸባርቀዋል።
የጦር ኀይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በበኩላቸው የሠራዊቱ የሪፎርም ሥራዎች እና የሰው ኀይል ግንባታ እያደገ መምጣቱን ገልጸዋል። የመከላከያ ሠራዊት የመዋጋት እና የቴክኖሎጂ አቅሙን በየጊዜው በማሳደግ አስተማማኝ የሀገር ጋሻ መኾኑንም አንስተዋል።
«ዛሬ ያቀናጀነው የመከላከያ ሠራዊታችን በምድር፣ በየብስም ኾነ በአየር የሚሰጠውን ማንኛውንም ወታደራዊ ግዳጅ በብቃት መወጣት የሚችልበት ደረጃ ላይ ደርሷል። የትኛውም የጠላት ኀይል የኢትዮጵያን ወሰን እና ደኅንነት ለመጣስ የሚያደርገውን ሙከራ ሙሉ በሙሉ የማክሸፍ ዝግጁነታችን አስተማማኝ ነው» ሲሉ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ አብራርተዋል።
የኢፌዴሪ አየር ኀይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ በበኩላቸው የኢትዮጵያ አየር ኀይል ከተሃድሶው ወዲህ ዘመናዊ አውሮፕላኖችን፣ የድሮን እና የራዳር ቴክኖሎጂዎችን በመታጠቅ የአየር ክልል የበላይነት ሙሉ በሙሉ መረጋገጡን ገልጸዋል።
«የኢትዮጵያ አየር ኀይል የሀገራችንን ሰማይ ሙሉ በሙሉ የመጠበቅ እና የመቆጣጠር ሙሉ ብቃት አለው፤ “ምድሩም፣ ሰማዩም፣ የብሱም የእኛ ነው” ስንል በተግባር በተረጋገጠ አቅም እና ዘመናዊ የጦር መሳሪያ ዝግጁነት ላይ ተመስርተን ነው። የአየር ክልላችን የተጠበቀ እና አስተማማኝ ነው» ብለዋል።
የሀገሪቱ አየር ኀይል የሰው ኀይል ሥልጠና እና የቴክኖሎጂ ዝግጁነት በማንኛውም ሰዓት እና ሁኔታ ፈጣን እና ወሳኝ እርምጃ ለመውሰድ በሚያስችል መልኩ የተቃኘ ነው። ይህ አስተማማኝ ወታደራዊ ቁመና የሀገሪቱ ደኅንነት እንዲጠበቅ እና በየትኛውም የጠላት ኀይል አይደፈሬ እንድትኾን ያደርጋታል።
ዛሬ ኢትዮጵያ የገነባችው የጸጥታ ተቋም የወቅቱን የቴክኖሎጂ ምጥቀት የተከተለ፣ የተቀናጀ እዝ ያለው እና የሀገርን ድንበር እና ሰላም በአስተማማኝ ሁኔታ መጠበቅ የሚያስችል ጠንካራ ወታደራዊ ቁመና ላይም ይገኛል።
ዘጋቢ፦ ቴዎድሮስ ደሴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
