
በኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ከሚሴ ከተማ በወቅታዊ የሰላም እና የልማት ጉዳዮች ዙሪያ ከከተማው ከተውጣጡ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር ምክክር ተካሂዷል።
በምክክር መድረኩ የከተማው ነዋሪዎች ሰላም የኹሉም ነገር መሠረት መኾኑን ጠቅሰው ዘላቂ ሰላም ለመፍጠር የበኩላቸውን እንደሚወጡም ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሟን ለማስከበር የምታረገውን ጥረት በመደገፍ ሉዓላዊነቷን ለማስከበር በጋራ ልንቆም ይገባልም ብለዋል።
በብልጽግና ፓርቲ የከሚሴ ከተማ አሥተዳደር ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ መሐመድ አሊ የልማት ሥራዎችን መከወን የሚቻለው ሰላም ሲረጋገጥ መኾኑን ጠቅሰው ዘላቂ ሰላም ለመገንባት ኅብረተሰቡ የድርሻውን ሊወጣ ይገባል ብለዋል።
በከተማው በሚሠሩ የልማት ሥራዎች የኅብረተሰቡ ተሳትፎ የላቀ መኾኑን በመጥቀስ በቀጣይም ማኅበረሰቡን የልማቱ አካል ለማድረግ ጥረት ይደረጋል ነው ያሉት።
የከሚሴ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ ሸሪፍ ቃሲም በበኩላቸው ሰላምን ማረጋገጥ ለመንግሥት ብቻ የሚተው ስላልኾነ ኹሉም የበኩሉን እንዲወጣም ጠይቀዋል።
የማኅበረሰቡን የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በበጀት ዓመቱ በትኩረት እንደሚሠራም አሥረድተዋል።
ዘጋቢ:- ይማም ኢብራሒም
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
