ኢትዮጵያ በልማት እና በሕዝቦቿ አንድነት ታላቅነቷን እያጸናች ትገኛለች።

6
ጥንታዊቷ ኢትዮጵያ በታሪኳ በርካታ የውስጥ እና የውጭ ፈተናዎችን በጽናት እና በጥበብ በማለፍ ነጻነቷን እና ታላቅነቷን አስከብራ የኖረች ሀገር ናት።
በኢትዮጵያ ፖሊሲ ጥናት ኢኒስቲትዩት ከፍተኛ ተመራማሪው ጀማል መሐመድ (ዶ.ር) ኢትዮጵያውያን በየዘመናቱ ሕልውናቸውን እና ሉዓላዊነታቸውን የሚፈታተኑ አጋጣሚዎች ሲገጥሟቸው ልዩነቶቻቸውን ወደ ጎን በመተው በአንድነት የመቆም ታሪካዊ ባሕል አላቸውም ብለዋል። የዚሁ የማይናወጥ የአንድነት እና የነጻነት ተጋድሎ ማሳያ የኾነው የዓድዋ ድል ዛሬም ቢኾን የትውልዱ ሕያው የጽናት እና የነጻነት ምልክት ኾኖ ቀጥሏል ይላሉ።
እንደ ዳግማዊ ዓድዋ የሚቆጠረው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሀገሪቱ በራሷ አቅም፣ ዕውቀት እና ገንዘብ አይበገሬነቷን ያስመሰከረችበት ታላቅ የታሪክ አሻራ እንደኾነም አስገንዝበዋል።
በአሁኑ ወቅትም ሀገሪቱ በመደመር እሳቤ እየተመራች የተፈጥሮ ጸጋዎቿን፣ የሰው ኀይሏን እና ታሪካዊ ሀብቶቿን አስተናብራ ለጋራ ብልጽግና በማዋል ላይ እንደምትገኝም ጠቁመዋል።
የዚህ ጥረት አካል የኾኑት የኮሪደር ልማት፣ የሌማት ትሩፋት፣ የገበታ ለሀገር እና ገበታ ለትውልድ ፕሮጀክቶች፣ ሀገሪቱን ከስንዴ ፈላጊነት ወደ ላኪነት ያሸጋገረው የግብርና ስኬት የሀገሪቱን ብሔራዊ አቅም ማደግ የሚያሳዩ ተጨባጭ ማረጋገጫዎች መኾናቸውን አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ በየዘመናቱ የሚያጋጥሟትን ወቅታዊ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ማዕበሎች፣ የውጭ ጫናዎችን እና የውስጥ ፈተናዎችን በልማት እና በአንድነት በማሸነፍ ላይ እንደምትገኝም አስገንዝበዋል።
ትክክለኛውን የዕድገት ጎዳና የያዘችው ሀገራችን ዛሬም በልጆቿ ብርቱ ክንድ እና በጽኑ መሠረቷ ላይ ቆማ ሉዓላዊነቷን በማጽናት እና የሕዝቦቿን የልማት መሻት በመፈጸም የታሪክ እና የከፍታ ጉዞዋን አጠናክራ ትቀጥላለች ነው ያሉት።
በምሥጋናው ብርሃኔ
‎
‎የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleትልቅ ሀገር፣ ትልቅ ሕዝብ፣ ታላቅ ርዕይ
Next articleለትልቅ ሀገር፣ ትልቅ ሕዝብ እና ለታላቅ ርዕይ የሚገባ ቀልጣፋ አገልግሎት።