
የወልድያ ከተማ አሥተዳደር በወቅታዊ የሰላም፣ የጸጥታ እና የልማት ጉዳዮች ዙሪያ ከከተማዋ የንግድ ማኅበረሰብ ጋር የምክክር መድረክ አካሂዷል።
በውይይቱ የተሳተፉት ነጋዴዎች የኅብረተሰቡን የኑሮ ጫና ለማቃለል እና የዋጋ ንረትን ለመቆጣጠር ቀዳሚ ኀላፊነታቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል። የከተማዋን ሰላም እና ልማት ለማስቀጠል የሚያደርጉትን አስተዋጽኦ አጠናክረው እንደሚቀጥሉም አረጋግጠዋል።
በምክክር መድረኩ ላይ የተገኙት የወልድያ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ዱባለ አብራሬ ከሰላም መደፍረስ የሚያተርፈው ስግብግብ ነጋዴ ነው ብለዋል። አላስፈላጊ የዋጋ ንረት የሚፈጥሩ አካላትን በራሳቸው የንግድ መዋቅር መታገል እና ማጋለጥ ከራሱ ከነጋዴው ማኅበረሰብ እንደሚጠበቅ ገልጸዋል።
የአማራ ክልል የሥነ ምግባር እና ጸረ-ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር ሀብታሙ ሞገስ ምርት እና ሸቀጥ በመደበቅ ኅብረተሰቡን በኑሮ ውድነት የሚያንገላቱ አካላት ሊታረሙ እና ሊስተካከሉ እንደሚገባ አሳስበዋል።
የንግዱ ማኅበረሰብ ከሐሰተኛ መረጃዎች ራሱን በማራቅ የከተማዋን ሰላም እና ጸጥታ በመጠበቅ ረገድ ሚናውን እንዲወጣም ጠይቀዋል።
የአማራ ክልል ፕላን ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ምትኩ ዓለማየሁ (ዶ.ር) ሀገር ለመበተን የሚሠሩ ኀይሎችን መቃወም የሀገርን ሕልውና የማስቀጠል ጉዳይ መኾኑን ገልጸዋል።
ሠርቶ ማደርም ኾነ ነግዶ ማትረፍ የሚቻለው ሰላም ሲኖር በመኾኑ የንግዱ ማኅበረሰብ የአካባቢውን ሰላም በማስከበር ረገድ ቁልፍ ድርሻውን መወጣት እንዳለበት አስገንዝበዋል።
