
ሦሥተኛው የሩሲያ – አፍሪካ ጉባኤ በሞስኮ ተካሂዷል።
በጉባኤው መልዕክት ያስተላለፉት የቡሩንዲ ፕሬዝዳንት እና የወቅቱ የአፍሪካ ኅብረት ሊቀ መንበር ኢቫሪስቴ ንዳይሺሚዬ በሞስኮ የተካሄደው ውይይት ስኬታማ ነበር ብለዋል።
በሩሲያ እና በአፍሪካ መካከል ያለውን ታሪካዊ የሰላም፣ የፍትሕ እና በመከባበር ላይ የተመሠረተውን ግንኙነት ማጠናከር እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች የአህጉሪቱን ዘላቂ ልማት ለማሳካት በሚያስችሉ ዘርፎች ላይ ትብብርን ለማጠናከር ዝግጁ ናቸው ብለዋል።
ሦሥተኛው የሩሲያ-አፍሪካ ጉባኤ የትብብራችንን ጥራት ለመለወጥ እና በፖለቲካዊ አንድነት ላይ ተመስርተን የኢኮኖሚ ትብብርን ለማጠናከር፣ የወጪ ንግድን ለመጨመር፣ በአህጉሪቱ እና በሩሲያ መካከል ያለውን ትብብር ለማሳደግ ዕድል ሰጥቶናል ነው ያሉት። ፍትሐዊ እና ዴሞክራሲያዊ የብዙ ወገን ዓለም አቀፍ ሥርዓት ለመገንባት በአንድነት እየሠራን ነውም ብለዋል።
አፍሪካ በጸጥታው ምክር ቤት እና በዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ውስጥ የተሻለ ውክልና እንዲኖራት እንድምትፈልግም አመላክተዋል።
የጸጥታው ምክር ቤት በተባበሩት መንግሥታት ሥር ለአፍሪካ ሰላም የበለጠ ግልጽ እና ፍትሐዊ ፋይናንስ እንዲኖር እንደሚሠሩም አንስተዋል።
የሩሲያ ባለሀብቶች ወደ አፍሪካ መጥተው ሊረዱን እና ኢንቨስት ሊያደርጉ ይገባል። እርስ በእርስ የሚጠቅም ትብብር ለመገንባት በአንድነት መሥራት አለብን ነው ያሉት። ይህ ጉባኤ በሁለቱም ወገኖች ላሉ ሕዝቦች የሚጠቅም እና የሚጨበጥ ውጤት እንደሚያስገኝ ተስፋ እናደርጋለንም ብለዋል።
አምራች ኢንቨስትመንቶችን እና የኢንዱስትሪ ምርቶችን ማሳደግ እንደሚገባም ተናግረዋል። የመሠረተ ልማት፣ የግብርና እና የኀይል ፕሮጀክቶች ግንባታን ማፋጠን፣ ሥልጠናን፣ ምርምርን እና የቴክኖሎጂ ሽግግርን ማጠናከር ይገባልም ነው ያሉት።
“ዘላቂ ልማት ሊረጋገጥ የሚችለው ሰላም እና ደኅንነት ሲጠበቅ ብቻ ነው” ያሉት ፕሬዝዳንቱ አፍሪካ አሁንም የጋራ ምላሽ፣ ከአካባቢያዊ ነባራዊ ሁኔታዎች ጋር የተጣጣሙ እና ዓለም አቀፍ ሕግን ያከበሩ መፍትሔዎችን የሚሹ የደኅንነት ስጋቶች እንደሚገጥሟት አንስተዋል።
ግጭቶችን የመከላከል፣ በሰላማዊ መንገድ የመፍታት፣ ሽብርተኝነትን፣ ጽንፈኝነትን የመዋጋት እና የአፍሪካ ተቋማትን አቅም የማጠናከር ጥረታችንን መቀጠል አለብንም ብለዋል።
የአፍሪካን ጥቅሞች ባከበረ መልኩ ከዓለም አቀፍ አጋሮች ጋር ያለውን ግንኙነት ማጠናከር እንደሚገባም አንስተዋል።
የአፍሪካ ኅብረት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቻርተር መሠረት ለውይይት፣ ለክልላዊ ትብብር እና ለባለብዙ ወገን ግንኙነት ቁርጠኛ መኾኑንም ገልጸዋል።
#የመደመር_መንግሥት!#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ! 🇪🇹
#ባሕር_ዳር #ጥቅምት_20_2019_ዓ_ም
✍️በታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
