“ጉባኤው የክልሉን የፍትሕ ሥርዓት ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር መልካም ተጽዕኖ ይኖረዋል” ዋና አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ

6
የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሁለተኛውን የዳኞች ዓመታዊ ጉባኤ “​የዳኝነት አገልግሎትን ማስፋት፣ አገልግሎትን ማላቅ” በሚል መሪ መልዕክት እየተካሄደ ነው።
በመክፈቻ መርሐ ግብሩ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የአማራ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ ​ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ባለፉት ሁለት ዓመታት ታላላቅ የሪፎርም ሥራዎችን ማከናወኑን ተናግረዋል።
ለአንድ ሀገር የፍትሕ ሥርዓት መጠናከር፣ ለሕግ የበላይነት መረጋገጥ እና ለዜጎች ሰብአዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብት መጠበቅ የዳኝነት ሥርዓቱ ሚና የጎላ ነው ብለዋል። በተለይም አማራ ክልል በልማት እና በኢንቨስትመንት ሳቢ እንዲኾን፣ ሰላም እና ዕድገትን ለማረጋገጥ የዳኝነት ሥርዓቱ መጠናከር ወሳኝ መኾኑንም አንስተዋል።
የዴሞክራሲ ሥርዓት የሚገነባው እና የሕግ የበላይነት የሚረጋገጠው በዳኝነት ሥርዓቱ ነው ያሉት ዋና አፈ ጉባኤዋ ለዚህ ስኬታማነት ነፃ፣ ገለልተኛ፣ በዕውቀት እና በክህሎት የዳበረ፣ በሥነ-ምግባር የታነፀ ዳኛ ማፍራት ወሳኝ ነው ብለዋል።
ትክክለኛ ፍትሕ ማግኘት የዜጎች መብት ነው ያሉት ዋና አፈ ጉባኤዋ ዳኞች የ​ዳኝነት ሙያዊ ነጻነታቸውን መሠረት በማድረግ ዜጎች ትክክለኛ ፍትሕ እንዲያገኙ እንዲሠሩም አሳስበዋል።
ዳኞች ሙያዊ ብቃታቸውን በተገቢው መንገድ በመጠቀም ሕዝብን እንዲያገለግሉ እና ያለአድልኦ ፍትሕን እንዲሰጡም አስገንዝበዋል።
የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤትም ሕጎችን በማሻሻል፣ የሥራ አካባቢን ምቹ እና ጽዱ በማድረግ፣ ተቋማትን በቴክኖሎጂ በማዘመን እና አገልግሎት አሰጣጥን በማሻሻል ከሌሎች ጋር ተቀናጅቶ ለመሥራት ያደረገው ጥረት በክልላችን ላሉ ተቋማት ትልቅ አርዓያ የሚኾን ነው ብለዋል።
ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ባለፉት ሁለት ዓመታት ላከናወናቸው ውጤታማ ተግባራትም የተቋሙ መሪዎች እና ሠራተኞች ምሥጋና ይገባቸዋል ነው ያሉት። “ጉባኤው የክልሉን የፍትሕ ሥርዓት ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር መልካም ተጽዕኖ ይኖረዋል” ብለዋል።
ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው
‎
‎የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleሕዳሴ – የትልቅ ሕዝብ፣ የትልቅ ሀገር እና የታላቅ ራዕይ ጽናት እና የተግባር ስኬት
Next articleዘላቂ ሰላምን ማጽናት እና የልማት ሥራዎችን ማስቀጠል ይገባል።