“የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤትን በሀገራችን እና በአፍሪካ ደረጃ ተምሳሌት ለማድረግ የሰነቅነው ርዕይ ፍሬ እያፈራ ነው” አቶ ዓለም አንተ አግደው

5
የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሁለተኛውን የዳኞች ዓመታዊ ጉባኤ “የዳኝነት አገልግሎትን ማስፋት፣ አገልግሎትን ማላቅ” በሚል መሪ መልዕክት እያካሄደ ነው።
የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ዓለምአንተ አግደው በዚህ ወቅት እንደተናገሩት የዳኞች ዓመታዊ ጉባኤ በክልሉ የሚገኙ ፍርድ ቤቶችን ለማጠናከር በወጣው አዋጅ መሠረት የክልሉን የዳኝነት አገልግሎት አሰጣጥ ለማላቅ እንዲያግዝ ታስቦ የተፈጠረ ተቋማዊ መድረክ ነው።
ባለፉት ሁለት የፍርድ ቤት የለውጥ ዓመታት ውስጥ የክልሉን ፍርድ ቤቶች ተቋማዊ ቁመና ለመገንባት በርካታ ተግባራት ተከናውነዋል ነው ያሉት። የዳኝነት ነፃነት እና ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ መሠረታዊ የለውጥ ሥራዎች ቅድሚያ ተሰጥተው ከተሠሩት ተግባራት መካከል የሚጠቀሱ ናቸው።
በጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ በከፍተኛ ፍርድ ቤቶች እና በአንዳንድ የወረዳ ፍርድ ቤቶች ለዳኞች፣ ለሠራተኞች፣ ለተገልጋዩ ኅብረተሰብ ምቹ የሥራ አካባቢ ለመፍጠር የተደረጉ ጥረቶችም ውጤታማ እንደነበሩ አንስተዋል።
የፍርድ ቤቶችን የአገልግሎት አሰጣጥ ለማሻሻል ዘመኑ በደረሰበት ቴክኖሎጂ የተደገፈ ለማድረግ ውጤታማ ተግባራት መከናወናቸውን ጠቁመዋል። ተግባራዊ በተደረገው የዲጂታላይዜሽን ሥራዎችም በክልሉ የዳኝነት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ትርጉም ያለው ለውጥ እየታየ ነው ብለዋል።
የቆዩ የፍትሕ አሥተዳደር ሥርዓት ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲሸጋገሩ የሚያድረግ እና ለተመራማሪዎች ጉልህ አስተዋጽኦ የሚያደርግ የፍትሕ ሙዚየም ተገምብቶ ለተጠቃሚዎች ክፍት መደረጉንም ገልጸዋል።
በባሕር ዳር ከተማ ሁሉ አቀፍ የፍትሕ ማዕከል ለመገንባት የተያዘው ዕቅድ እውን በመኾን ላይ ይገኛልም ነው ያሉት። ለማዕከሉ ግንባታ 25 ሄክታር መሬት በጣና ሐይቅ ዳር ላይ ቦታ ተረክበን ለተነሺዎች ካሳ ተከፍሎ ቦታው ለግንባታ ዝግጁ እንዲኾን ተደርጓልም ብለዋል።
በቀጣይ አንድ ወር ጊዜ ውስጥም ግንባታው እንደሚጀመርም አስታውቀዋል። “የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤትን በሀገራችን እና በአፍሪካ ደረጃ ተምሳሌት ለማድረግ የተሰነቀው ርዕይ ፍሬ እያፈራ ነው” ብለዋል ፕሬዝዳንቱ።
ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው
‎
‎የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous article“ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ያከናወናቸው ሥራዎች ለሌሎች ተቋማትም በአርዓያነት የሚጠቀስ ነው” ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው
Next articleለትልቅሀገር፣ ለትልቅ ሕዝብ እና ለታላቅ ርዕይ የሚመጥነው የኢትዮጵያ የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም።