“ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ያከናወናቸው ሥራዎች ለሌሎች ተቋማትም በአርዓያነት የሚጠቀስ ነው” ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው

8

 

የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሁለተኛውን የዳኞች ዓመታዊ ጉባኤ “​የዳኝነት አገልግሎትን ማስፋት፣ አገልግሎትን ማላቅ” በሚል መሪ መልዕክት ማካሄድ ጀምሯል።

በመክፈቻው ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ያከናወናቸው የዲጂታላይዜሽን ሥራዎች ለሌሎች ተቋማትም በአርዓያነት የሚጠቀስ ነው ብለዋል።

ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ዘመኑን የዋጀ የፍትሕ አሰጣጥ እና የዳኝነት ሥርዓት ለመገንባት የሚያደረገው ጥረት ትልቅ ቦታ የሚሰጠው መኾኑን ገልጸዋል። የፍርድ ቤትን ክብር ያስጠበቀ እና ለሕዝብ የቀረበ ተቋም ለመኾን እያከናወናቸው ያሉት ተግባራትም የሚደነቅ መኾኑን አንስተዋል።

​ባሕር ዳር ከተማን ዘመናዊ እና ስማርት ከተማ ለማድረግ ከምንሠራቸው ተግባራት መካከል አንዱ ዲጂታላይዜሽን ነው ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ለዚህም ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ በአርዓያነት ሠርቶ ማሳየቱን ጠቁመዋል።

በዚህም ለባሕር ዳር ከተማ ዲጂታላይዜሽን ሥራዎች አንዱ መገለጫ ኾኖ እየመጣ ያለው የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ እና በወረዳ ፍርድ ቤቶች እየተሠራ ያለው ዲጂታላይዜሽን በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀስ መኾኑን ጠቁመዋል።

በተጨማሪም ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የከተማዋን የኮሪደር እና የጣና ዳር ልማት ፕሮጀክቶችን የጋራ ሥራ አድርጎ በመጋራት ሞዴል ኾኖ ያሳየ መኾኑን አመላክተዋል።

ባሕር ዳር ከተማ እንደ ወትሮው ሁሉ ሰላሟን አስጠብቃ ልማት እየለማባት ያለች ከተማ ናት ብለዋል። ባሕር ዳር ከተማ ከኮሪደር ልማት በተጨማሪ ኢንዱስትሪዎች እና ሌሎችም ተስፋ ሰጭ የልማት ሥራዎች ተሠርተዋል ብለዋል። የጉባኤው ተሳታፊዎች ከተማዋን ተዘዋውረው እንዲጎበኙም ጋብዘዋል።

#ትልቅ_ሀገር #ትልቅ_ሕዝብ #ታላቅ_ርዕይ

#ባሕር_ዳር #መስከረም-20_2019_ዓ_ም

✍️ ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው

የአሚኮ ዲጂታል ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleበአማራ ክልል የግሪሳ ወፍ በሰብል ላይ ያደረሰውን ጉዳት ለመቆጣጠር የተቀናጀ የመከላከል ሥራ እየተከናወነ ነው።
Next article“የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤትን በሀገራችን እና በአፍሪካ ደረጃ ተምሳሌት ለማድረግ የሰነቅነው ርዕይ ፍሬ እያፈራ ነው” አቶ ዓለም አንተ አግደው