በአማራ ክልል የግሪሳ ወፍ በሰብል ላይ ያደረሰውን ጉዳት ለመቆጣጠር የተቀናጀ የመከላከል ሥራ እየተከናወነ ነው።

11

 

በአማራ ክልል በሚገኙ አራት ዞኖች የግሪሳ ወፍ መንጋ በደረሱ ሰብሎች ላይ ጉዳት እያደረሰ እንደሚገኝ የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታውቋል።

በግብርና ሚኒስቴር የእጽዋት ጥበቃ መሪ ሥራ አሥፈጻሚ የተቀናጀ ተባይ መከላከል ባለሙያ ውባንተ ግርማ እንደገለጹት ከአየር ንብረት ለውጥ (ኤልኒኖ) ጋር ተያይዞ ዘንድሮ የተከሰተው የወፍ መንጋ ጉዳት ከዚህ ቀደም ከተከሰቱት ሁሉ የከፋ ነው።

የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የሰብል ልማት እና ጥበቃ ዳይሬክተር ማንደፍሮ አስላከ (ዶ.ር) እንዳመለከቱት የግሪሳ ወፉ በሰሜን ሸዋ፣ በኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር፣ በሰሜን ወሎ እና በደቡብ ወሎ ዞኖች ስር ባሉ 14 ወረዳዎች በሚገኙ 56 ቀበሌዎች ተሰራጭቷል።

እስካሁን በተካሄደው የመከላከል ዘመቻ በ494 ሄክታር መሬት ላይ 988 ሊትር ኬሚካል በመርጨት የግሪሳ ወፍ ማስወገድ ተችሏል። ከጉዳቱ ስፋት አንጻር የሰሜን ሸዋ ዞን ተጠቃሽ ነው።

በሰሜን ሸዋ ዞን ግብርና መምሪያ የሰብል ጥበቃ ተወካይ ባለሙያ አፈወርቅ ታደሰ እና በቀወት ወረዳ የግብርና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ቅጣው ኃይሌ እንደተናገሩት የወፍ መንጋው በምንጃር፣ በአንፆኪያ፣ በኤፍራታ እና ግድም፣ በቀወት ወረዳዎች፣ በሸዋሮቢት ከተማ አሥተዳደር፣ በአጎራባች የጣርማበር፣ አንኮበር እና በረኸት ወረዳዎች በመንቀሳቀስ በደረሱ የማሽላ እና የጤፍ ሰብሎች ላይ ጉዳት እያደረሰ ይገኛል።

የወፉ ቁጥር እና የማደሪያው ስፋት መጨመር ባሕላዊ የመከላከል ሥራውን አስቸጋሪ አድርጎታል። እስካሁን በዞኑ በሚገኙ 237 ነጥብ 5 ሄክታር ማደሪያዎች ላይ 475 ሊትር ኬሚካል ተረጭቷል።

የመከላከል ሥራውን በላቀ ደረጃ ለማከናወን ከአየር ላይ የኬሚካል ርጭት ሥራ እየተካሄደ ይገኛል። ለዚህም በሸዋሮቢት ከተማ የተዘጋጀው የአውሮፕላን መንደርደሪያ በኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ተረጋግጦ ለአገልግሎት ዝግጁ ኾኗል። በአጭር ጊዜ ውስጥ ሥራ እንደሚጀምር ተገልጿል።

ሰብሉ ተሠብሥቦ ወደ ጎተራ እስኪገባ ድረስ ተጨማሪ አውሮፕላኖችን በመመደብ የመከላከል ዘመቻው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተመላክቷል። ከአየር ላይ ርጭቱ ጎን ለጎን ኅብረተሰቡ የሚያደርገው ባሕላዊ የመከላከል እንቅስቃሴም ትኩረት ተሰጥቶት ሊሠራ እንደሚገባ ተገልጿል።

#ታላቅ_ሀገር_ታላቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ

#የግሪሳወፍ_መከላከል #አማራክልል #አሚኮ ኢትዮጵያ🇪🇹

#ባሕር_ዳር #መስከረም_20_2019_ዓ_ም

ዘጋቢ፦ የደጀኔ በቀለ
‎
‎የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleለትልቅ ሀገር፣ ትልቅ ሕዝብ እና ታላቅ ራዕይ የሚገባ የባሕር በር🇪🇹
Next article“ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ያከናወናቸው ሥራዎች ለሌሎች ተቋማትም በአርዓያነት የሚጠቀስ ነው” ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው