
ኢትዮጵያ በታሪኳ በባሕር እና በየብስ ላይ ታላቅ ሥልጣኔዋን የገነባች፣ ሉዓላዊነቷንም በምድር እና በባሕር ኃይሏ አስከብራ የኖረች ታላቅ ሀገር ናት።
ከቀይ ባሕር እስከ ኤደን ባሕረ ሰላጤ ድረስ የነበራት የባሕር ንግድ እና የባሕር ኃይል የበላይነት ሀገራችን የገዘፈ አቅም እንደነበራት የሚያሳይ ነው። የአክሱም ሥልጣኔ በየብሱ ብቻ ሳይኾን በባሕር ላይም ገዥ እንደነበረ የታሪክ መዛግብት ምስክሮች ናቸው።
የቀድሞው የባሕር ኃይል ባልደረባ እና የፖለቲካል ሳይንስ ምሁሩ ሌፍተናንት ኮማንደር መረባ አቶምሳ ታሪክ ተደምስሶ ኢትዮጵያ ከባሕር በሯ እንድትገለል እና ለአንድ ትውልድ ያህል በመልክዓምድራዊ እስር ቤት ውስጥ እንድትቆይ የተደረገችው በውስጥ እና በውጭ ፖለቲካዊ ሴራዎች ምክንያት ነው ብለዋል።
ነገር ግን ያ! የጨለማ ዘመን አብቅቷል! ዛሬ ኢትዮጵያ የቀደመ ታሪካዊ እና ተፈጥሯዊ መብቷን ለማስመለስ፣ ያንን የታሰረችበትን የጂኦግራፊ እስር ቤት በጽናት እና በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ሰብራ ለመውጣት እየሠራች ትገኛለች ነው ያሉት።
ዓላማዋም ግልጽ ነው፤ በአፍሪካ ቀዳሚዋ የኢኮኖሚ ባለቤት መኾን እና በዓለም ግዙፍ ኢኮኖሚ ካላቸው ሀገራት ተርታ መሰለፍ ነው ብለዋል።
ታዲያ ይህን ታላቅ ርዕይ ለማሳካት የባሕር በር ማግኘት የሞት እና የሽረት ጉዳይ በመኾኑ የተጀመረው እንቅስቃሴ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ምሁሩ አስምረውበታል።
የባሕር በር ጥያቄ ከትራንስፖርቴሽን አገልግሎት በላይ የኢኮኖሚ ህልውና ጉዳይ መኾኑን የተናገሩት ደግሞ የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ መምህሩ መሐመድ ሲራጅ (ዶ.ር) ናቸው።
ቀይ ባሕር የዓለም ገበያ ዋና መዳረሻ በመኾኑ የባሕር በር ማጣት በኢትዮጵያ ንግድ፣ በውጭ ኢንቨስትመንት እና በሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ ትልቅ ጥላ ጥሏል ብለዋል።
ሀገሪቱ ለወደብ ኪራይ ከምታወጣው ከፍተኛ ወጪ በተጨማሪ ወደ ሀገር በሚገቡ የፍጆታ ዕቃዎች ላይ ከ30 በመቶ በላይ ዋጋ እንዲጨመር በማድረግ የሕዝቧን የኑሮ ውድነት አባብሶታል ነው ያሉት። የባሕር በር ባለቤት መኾን ግን ይህንን ሁሉ ምስቅልቅል ይቀይረዋል ነው ይላሉ ምሁሩ።
በየዓመቱ ለወደብ አገልግሎት የሚወጣውን በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር በማስቀረት እንደ ሕዳሴው ግድብ ያሉ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን በራሳችን አቅም ለመገንባት ያስችላል፤ የወጪ እና ገቢ ንግዱ ሲቃለል የውጭ ኢንቨስትመንት በስፋት ይጎርፋል፤ ይህም ለሚሊዮን ወጣቶች የሥራ ዕድል ይፈጥራል ብለዋል።
በመኾኑም ኢትዮጵያ የጀመረችውን የባሕር በር የማስመለስ ጉዞ አጠናክራ ማስቀጠል እንዳለባት ነው የተናገሩት።
#ታላቅ_ሀገር #ታላቅ_ሕዝብ #ታላቅ_ርዕይ
#ባሕር _ዳር #መስከረም-20_2019_ዓ_ም
✍️ ዘጋቢ፦ ቴዎድሮስ ደሴ
የአሚኮ ዲጂታል ቤተሰብ ይሁኑ!
