መሠባሠቢያ ቤታችን፤ ደምቆ መታያ ውበታችንን እንጠብቅ።

24
የዓለም እግር ኳስ መድረክ በክህሎት ብቻ ሳይኾን በስፖርታዊ ጨዋነት እና በሥነ-ምግባር ጭምር የሚደምቅበት ዘመን ላይ እንገኛለን። ለዚህ ደግሞ የጃፓን ብሔራዊ ቡድን ደጋፊዎች በዓለም ዋንጫ መድረኮች ላይ ያሳዩን ልብ የሚነካ ተሞክሮ ሕያው ማሳያ ይኾነናል።
የጃፓን ብሔራዊ ቡድን ደጋፊዎች ብሔራዊ ቡድናቸው ቢያሸንፍም፤ ባያሸንፍም 90 ደቂቃው ሲጠናቀቅ የያዙትን ፌስታል አውጥተው የተቀመጡበትን ስታዲየም እያንዳንዱን ፍርፋሪ እና ቆሻሻ አንዳች ሳያስቀሩ ሲያጸዱ ዓለም በታላቅ አክብሮት ተመልክቷቸዋል።
ይህ ተግባራቸው ስታዲየምን እንደ ራስ ቤት የመንከባከብ፣ ለባሕል እና ለሥርዓት የመገዛት ታላቅ የዜግነት መገለጫ ተደርጎም በታሪክ ተመዝግቦላቸዋል።
ታዲያ ዛሬ የታላቅ ዓለም አቀፍ ስታዲየም ባለቤት የኾኑት ኢትዮጵያውያን ደግሞ ይህንን ድንቅ አርዓያነት ወደ ራሳቸው አምጥተው የሚተገብሩበት ታሪካዊ ቀን ላይ እንገኛለን።
ማራኪዋ እና ውቧ ባሕር ዳር ከተማ ሌላ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ከፍታለች። ለብዙ ዓመታት በጉጉት ሲጠበቅ የነበረውን እና ግንባታው ዓለም አቀፍ ደረጃውን ጠብቆ የተጠናቀቀው የባሕር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም የመጀመሪያውን የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ በደመቀ ሁኔታ አስተናግዷል።
ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረክ ጨዋታዎችን እንድታደርግ እና ክብሯን እንድታስጠብቅ ትልቅ በር የከፈተው ይህ ዘመናዊ ዓለም አቀፍ ስታዲየም እግር ኳስ ወዳዱ ማኅበረሰብ ጥራቱን እና ውበቱን በይፋ የተመለከተበት ልዩ አጋጣሚ ተፈጥሯል።
ታሪካዊውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እና የሴኔጋል ብሔራዊ ቡድን ጨዋታ ለመታደም ወደ ስታዲየሙ የገባው ስፍር ቁጥር የሌለው የዋልያዎቹ ደጋፊ ገና ወደ ግቢው ሲዘልቅ በፊቱ ላይ ይነበብ የነበረው የደስታ ስሜት እጅግ አስደናቂ ኾኖ ታይቷል።
ኢትዮጵያ በታሪኳ እንደዚህ ዓይነት የተሟላ፣ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ እና እጅግ ጥራት ያለው ስታዲየም ስታገኝ የመጀመሪያዋ በመኾኑ እያንዳንዱ ደጋፊም በአድናቆት እና በከፍተኛ መገረም ዙሪያ ገባውን ሲመለከት ተስተውሏል።
“ይህ በእርግጥ የእኛ ስታዲየም ነው?” የሚያስኝ የኩራት ስሜት በደጋፊው ልብ ውስጥ ሲመላለስ በስታዲየሙ ውበት ተስፋው እና ደስታው ሲያብብ በግልጽ ይታይም ነበር። ይህ የሕዝቡ የደስታ ስሜት እና ለስፖርቱ ያለው ፍቅር ስታዲየሙ ብሎም ስፖርቱ ምን ያህል የተናፈቀ ታላቅ ሃብት መኾኑን ያረጋገጠ ኾኗል።
ይሁን እንጂ ይህንን ለዐይን የሚማርክ እና የሀገር ኩራት የኾነውን አዲስ ስታዲየም ማግኘት ብቻውን በቂ እንዳልኾነ መገንዘብ ያስፈልጋል። ትልቁ እና ዋናው ቁምነገር ይህንን ሃብት ተንክባክቦ ለትውልድ ማሻገር ላይ ነው።
ደጋፊው የመጀመሪያውን ጨዋታ በሥርዓት እና በጥንቃቄ ተመልክቶ እንደወጣው ሁሉ ወደፊትም ከንጽሕና እስከ ደኅንነት የስታዲየሙን ወንበሮች፣ መብራቶች፣ የሣር ሜዳውን እና ሌሎች የስታዲየሙ ክፍሎች እንዳይጎዱ እንደ ዐይኑ ብሌን ሊጠብቃቸው ይገባል።
በሌላ በኩል ጨዋታው ሲጠናቀቅ ደጋፊው የሚይዛቸውን ቁሳቁሶች እና ቆሻሻዎች በአግባቡ በማንሳት ስታዲየሙ ሁልጊዜም በአዲስነቱ እንዲቀጥል ማድረግ የሁሉም የቤት ሥራ መኾን አለበት። ስታዲየሙን እንደ ራስ ቤት በማየት እያንዳንዱን ጨዋታ በሥርዓት በመመልከት እና ንጽሕናውን በመጠበቅ እንደ ጃፓን ደጋፊዎች ታሪካዊ አሻራችንን ልናሳርፍ ይገባል።
ደጋፊው ወደ ስታዲየም ሲገባ እና ሲወጣ መገፋፋት ሳይኖር በተረጋጋ ሁኔታ ወረፋን ጠብቆ በመግባትም ራሱን ከአካል ጉዳት ከመከላከል አልፎ የስታዲየሙን ሃብቶች ደኅንነት መጠበቅ እንዳለበትም ይታመናል።
የኢትዮጵያውያን መሠባሠቢያ ቤታችን፣ ደምቆ መታያ ውበታችን የኾነውን ታላቁ የባሕር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየምን በጥንቃቄ እንጠብቅ !።
በአድኖ ማርቆስ
‎
‎የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleለክልሉ ሰላም በጋራ መቆም ያስፈልጋል።
Next articleቃል በተግባር በጣና ዳርቻ፦ የባሕር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም