
ባሕር ዳር: መስከረም 20/2019 ዓ.ም (አሚኮ) በዚህ ዓመት የተከሰተው ኢልኒኖ ከፍተኛ የዝናብ መዛባትን እና የድርቅ ሥጋትን ፈጥሯል።
ይህም በምግብ ዋስትና ላይ ትልቅ ተጽዕኖ እንደሚደቅን የዓለም ሜትሮሎጂ ድርጅትን ጨምሮ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት እየገለጹ ነው።
ታዲያ ኢትዮጵያስ ይህንን ተፈጥሯዊ ተጽዕኖ ለመቋቋም ምን ቅድመ ጥንቃቄ እያደረገች ይኾን? በኢትዮጵያ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን የሰብአዊ ድጋፍ በራስ አቅም ማስተባበሪያ መሪ ሥራ አስፈጻሚ አሻግሬ ተሾመ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የተፈጥሮ አደጋዎች የሚከሰቱበት የጊዜ ዑደት እየጠበበ መጥቷል ብለዋል።
ከዚህ ቀደም አደጋዎች በየ10 እና 15 ዓመታት ልዩነት ይከሰቱ ነበር። አኹን ላይ ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያይዞ የጊዜ ዑደቱ ወደ ሦስት እና አምስት ዓመታት ዝቅ ብሏል ነው ያሉት።
እየጨመረ የመጣውን የሥጋት መጠን ለመቋቋም ሲባልም የኢትዮጵያ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ከፌደራል እና ከክልል ተቋማት ጋር በመቀናጀት የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን ስለመጀመራቸውም አንስተዋል።
አኹን በተፈጠረው የኢልኒኖ ተፅዕኖ ምክኒያት በሀገር አቀፍ ደረጃ በተደረገው ቅድመ ግምገማ በ10 ክልሎች የሚገኙ 178 ወረዳዎች ለጉዳት ተጋላጭ ኾነው ተለይቷል አሉን።
ከእነዚህም ውስጥ 88 ወረዳዎች በከፍተኛ የዝናብ እጥረት ጉዳታቸው የጎላ እንደሚኾን ጠቁመዋል። በአንጻሩ ዘገይተውም ቢኾን ዝናብ ባገኙ አካባቢዎች የተጎዱ ሰብሎችን መልሶ የመዝራት ሥራ እየተከናወነ ይገኛል። የእንስሳት መኖ ማሠራጨት እና የውኃ አቅርቦት ሥራዎችም እየተሠሩ ነው እንደ ኃላፊው ገለጻ።
የአደጋ ሥጋት ምላሽ ፈንድ ተቋቁሞ ባለፉት ስድስት ወራት 15 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ከዜጎች እና ከተቋማት ተሰብስቧል። ከተሰበሰበው ገንዘብ ውስጥ 4 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር ለአስቸኳይ እህል ክምችት እንዲውል ተደርጎ ግዢ ጭምር እየተፈጸመ ይገኛል ብለዋል አቶ አሻግሬ።
በቀጣይ በፌደራል፣ በክልል እና በታችኛው መዋቅር መካከል ያለው የመረጃ እና የድጋፍ ፍሰት የተናበበ ኾኖ እንዲቀጥል እየተሠራ ይገኛልም ብለዋል። በየደረጃው የሚገኘው ኅብረተሰብ የነባር መደጋገፍ ሥርዓቶችን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ አሳስበዋል።
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይኹኑ!
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
