
የመስቀል በዓል በአማራ ክልል ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን፤ በሁመራ ከተማ ተከብሯል። የሰቲት ሁመራ ዞን ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አሥኪያጅ መጋቢ ሐዲስ መምህር ዜናዊ አሸተ መስቀል ለበርካታ ዘመናት ተቀብሮ መቆየቱን እና በንግሥት ዕሌኒ ዘመን ተቆፍሮ መገኘቱን ገልጸዋል።
የመስቀሉ መቀበር እና መገኘት በዘመናት መካከል የሚያጠፋ እና በሌላ ዘመን ደግሞ የሚያለማ ትውልድ ስለመኖሩ ታላቅ ማሳየ ነው ብለዋል።
የአሁኑ ዘመን ትውልድም መስቀሉን እንደቀበሩት ሳይኾን ቆፍረው እንዳገኙት ትውልዶች ለሀገር ሰላም፣ አንድነት እና ልማት ቁርጠኛ መኾን እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የዞኑ ዋና አሥተዳዳሪ አሸተ ደምለው የደመራ እና የመስቀል በዓል የሃይማኖት እና የተስፋ ምልክት ነው ብለዋል። የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ሕዝብም ለበርካታ ዘመናት የተነጠቀውን ነጻነት እና ማንነት ማረጋገጥ መቻሉን አጣቅሰዋል።
በጋራ ትግል፣ መስዋዕትነት፣ ትብብር እና ኅብረት የተረጋገጠውን ወሰን እና ማንነት ለማስቀጠል ሕዝብ እና መንግሥት ተቀናጅተው እየሠሩ መኾናቸውንም ጠቁመዋል።
የበዓሉ ተሳታፊዎችም በዓሉ ከንግሥት ዕሌኒ እምነት እና ጽናትን የምንማርበት ነው ብለዋል። ሕዝበ ክርስቲያኑ በዓሉን በፍቅር እና በአንድነት እያከበረ ማስቀጠሉንም አንስተዋል።
#አሚኮ #መስቀል #Ethiopian ✝️🇪🇹
#ሁመራ #መስከረም_17_2019_ዓ_ም
✍️ በአምሳሉ አሞኘ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
