
የመስቀል በዓል በታሪካዊቷ ጎንደር ከተማ በድምቀት ተከብሯል።
በበዓሉ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የማዕከላዊ ጎንደር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ብጹዕ አቡነ ዮሐንስ መስቀል አስቀድሞ የተሰጠ የድኅነት ምልክት መኾኑን ገልጸዋል።
መስቀል ዓለም አቀፍ የቤተ ክርስቲያን ምልክት፣ የክርስትና አርማ ነው፤ በተለይም በኢትዮጵያ ምልክትነቱ ከፍ ያለ ነው ብለዋል። ቀሳውስቱ በእጃችን መስቀል እንይዛለን፣ እናቶቻችን ደግሞ መስቀል ጌጣቸው ነው ያጌጡበታል፤ በአንገታቸው ያሥሩታል ነው ያሉት።
የመስቀል ምልክት በኢትዮጵያ ቀኖናዊም ባሕላዊውም ነው ብለዋል። ቀኖናዊነቱ ቤተክርስቲያን ከታነጸ ከጉልላቱ ላይ መስቀል መኖር አለበት፤ መስቀል ከሌለበት ቤተክርስቲያን ሊባል አይችልም ነው ያሉት።
ባሕላዊነቱ ደግሞ በየልብሶቻችን እና በልዩ ልዩ ሁኔታዎች የሚታየው መኾኑ ነው ብለዋል። ባሕሉ መንፈሳዊነት ስላለው ሊደገፍ የሚገባው የሚያኮራ ባሕል መኾኑንም አንስተዋል።
መስቀል ዓለምአቀፋዊነት ምልክቱ የጎላው ጥንት
መስቀል የእርግማን ምልክት ስነበር፤ ዛሬ ግን የበረከት ምልክት ስለኾነ ነው ብለዋል። መስቀል የበረከት መገኛ መኾኑንም ገልጸዋል። መስቀል ጥንት የውርደት ምልክት ነበር፤ አሁን ግን የክብራችን ምልክት ነው፣ በመስቀል እንመካበታለን ነው ያሉት።
መስቀል በድሮ ዘመን የጥል ምልክት ነበር፤ ዛሬ ግን የሰላም ምልክት ነው፤ መስቀል የባርነት ምልክት ነበር፣ ዛሬ ግን የነጻነት ምልክት ነው፤ ክርስቶስም በመስቀል ነጻ አውጥቶናል ነው ያሉት።
የተደበቀውን እና የተቀበረውን መስቀል ንግሥት ዕሌኒ ማውጣቷን ገልጸዋል። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ይህን ታሪክ ይዛ በዓሉን እንደምታከብርም አንስተዋል።
በዓሉን ስናከብር ስለ ሀገራችን ሰላም እየጸለይን፣ ድሆችን እየረዳን እና በትህትና እየታዘዝን መኾን አለበት ነው ያሉት።
#አሚኮ #መስቀል #ኢትዮጵያ🇪🇹
#ባሕር_ዳር #መስከረም_17_2019_ዓ_ም
በታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
