
የመስቀል በዓል በታሪካዊቷ ጎንደር ከተማ በድምቀት ተከብሯል።
በበዓሉ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የማዕከላዊ ጎንደር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ዮሐንስ፣ የቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ፣ የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘውን ጨምሮ ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች፣ የቤተክርስቲያን ሊቃውንት እና አማኞች ተገኝተዋል።
በበዓሉ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው ዛሬ በዚህ ታላቅ አደባባይ ስንሠበሠብ ከአባቶቻችን የወረስነውን ታላቅ አደራ እናስታውሳለን ብለዋል።
ንጉሥ ዳዊት በፍቅር የተቀበለውን ቅዱስ መስቀል ወደ ሀገሩ ለማስገባት የጀመረውን ታሪካዊ ጉዞ ልጁ አጼ ዘርዓያቆብ ፍጻሜ አበጅቶለት በግሸን ደብረ ከርቤ አኑሮታል ነው ያሉት።
መስቀል ሃይማኖታዊ እሴቱ የጎላ ነው፣ ወድቆ መነሳትን፣ መስዋዕትነትን እና ፍቅርን የሚያስተምር መኾኑንም ገልጸዋል። መስቀል የአንድነታችን ታላቅ አደባባይ ነውም ብለዋል። የመስቀል ታሪክ በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ ተስፋን የማየት ምስጢር መኾኑንም ተናግረዋል።
በቀደምት ሮማውያን ዘንድ የወንጀለኞች መቅጫ የነበረው መስቀል ክርስቶስ ከተሰቀለበት በኋላ ሙታንን ሲያስነሳ እና ሕሙማንን ሲፈውስ ያዩ አይሁዳውያን በቅናት ተሞልተው በጉድጓድ ቀብረውት፣ ለ300 ዓመታት ቆሻሻ ሲደፋበት ቆዬ፣ ንግሥት ዕሌኒ ሳትታክት ባደረገችው ፍለጋ የመስቀሉን ቦታ አገኘች፤ አውነተኛውን መስቀልም አወጣች ነው ያሉት።
ይህ ታሪክ እውነት እና ፍቅር በቆሻሻ ተራራ ቢሸፈኑ እንኳን በጽናት እና በትዕግሥት ከተፈለጉ በብርሃን እንደሚወጡ ያስተምረናል ብለዋል።
በትዕግሥት እና በፍቅር ተንቀሳቅሰን ጥላቻን እና መለያያትን ማስወገድ፣ የተሸሸገውን አብሮነታችንን እና አንድነታችን ማደስ አለብን ነው ያሉት።
የዓለም የቱሪዝም ቀን በታሪካዊቷ ጎንደር እንዲከበር መመረጡ ለእኛ ክብር ነው፤ ጥንታዊ ቅርሶቻችንን፣ ሃይማኖትን እና ባሕላችንን ለዓለም ለማስተዋወቅ እና የቱሪዝም እንቅስቃሴን ለማነቃቃት ትልቅ ዕድል ነው ብለዋል።
ጥላቻን፣ መለያየትን እና ግጭትን የዚህ ዘመን ቆሻሻዎች አድርገን በመቁጠር በጋራ አጽድተናል፤ ጎንደርን የሰላም እና የፍቅር ማዕከል አድርገናታል ነው ያሉት።
የተገኘው ሰላም ለከተማዋ ልማት መፋጠን መሠረት መኾኑንም ገልጸዋል። የዛሬው ትውልድ ከአባቶቹ የወረሰውን ሃይማኖት፣ ፍቅር እና አደራ በትህትና ሊጠብቀው እንደሚገባም አስገንዝበዋል። ፍቅር የማይንቀሳቀስ ነገር ግን ሁሉን አንቀሳቃሽ ታላቅ ኀይል ነው፤ ዛሬም በጋራ ተንቀሳቅሰን የተደበቀውን የጥንት ፍቅራችንን እንፈልግ ብለዋል።
#አሚኮ #መስቀል #ኢትዮጵያ🇪🇹
#ባሕር_ዳር #መስከረም_17_2019_ዓ_ም
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
