
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በዓደባባይ ከምታከብራቸው ታላላቅ በዓላት አንዱ የኾነው የመስቀል ደመራ በዓል በምዕራብ ጎንደር ዞን በገንዳ ውኃ ከተማ በልዩ ልዩ ሃይማኖታዊ እና ባሕላዊ ሥነ ሥርዓቶች ተከብሯል።
በበዓሉ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የምዕራብ ጎንደር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ብጹዕ አቡነ ሰላማ የመስቀል በዓል የጨለማ መገፈፍ፣ የብርሃን መፈንጠቅ እና የጽናት ማሳያ መኾኑን ገልጸዋል።
ነገረ መስቀሉ ሲታሰብ ታሪኩን ሰምቶ ከመሄድ ባለፈ ቃሉን መተግበር እና መልካም ሥራዎችን መሥራት እንደሚገባ ያሳሰቡት ብጽዕነታቸው ምዕምናን በዓሉን በመተሳሰብ እና በመከባበር እያከበሩ ለሀገር ሰላም በጋራ እንዲጸልዩም ጥሪ አቅርበዋል።
የምዕራብ ጎንደር ዞን ባሕል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት መምሪያ ተወካይ ዓለሙ ጌታቸው የመስቀል ደመራ በዓል ቱሪዝምን ለማሳለጥ ያለው ድርሻ ከፍተኛ መኾኑን ጠቁመዋል። የዓደባባይ በዓላት ሲከበሩ ማኅበረሰቡ የአለባበስ ሥርዓቱን፣ ሃይማኖታዊ ባሕሉን እና ትውፊቱን ጠብቆ እንዲያከብር በርካታ ሥራዎች መከናወናቸውንም አብራርተዋል።
የገንዳ ውኃ ከተማ አሥተዳደር ተወካይ ከንቲባ አዳነ ሀሰን አባቶቻችን ደመራ ደምረው ጨለማውን በብርሃን እንዳሸነፉ ሁሉ፤ እኛም አብሮነታችንን በማጠናከር ለከተማችን እድገት እና ብልጽግና በጋራ የምንቆምበት ወቅት ነው ብለዋል።
ማኅበረሰቡ ደመራውን ሲለኩስ ብሔር፣ ቋንቋ እና ሃይማኖት ሳይገድበው ለአካባቢው እና ለሀገሩ ብርሃንን፣ ልማትን እና እድገትን እያሰበ በጠንካራ አብሮነት ሊያከብረው እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የበዓሉ ታዳሚዎች በበኩላቸው የመስቀል ደመራ በዓልን የኢየሱስ ክርስቶስን ስቃይ እና መከራ በማሰብ እያከበሩት እንደሚገኙ ገልጸዋል። ለሀገር ሰላም በመጸለይ፣ የአብሮነት፣ የመከባበር እና የመተሳሰብ እሴቶችን በማሳደግ በዓሉን እንደሚያሳልፉም ተናግረዋል።
#አሚኮ #መስቀል #ኢትዮጵያ🇪🇹
#ገንዳ_ውኃ #መስከረም_17_2019_ዓ_ም
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
