
ኢትዮጵያውያን ያላቸውን የካበተ የማይዳሰስ ቅርስ አጥብቀው መጠበቅ እና መንከባከብ እንዳለባቸው በታሪካዊቷ ጎንደር ከተማ የመስቀል በዓልን የታደሙ የውጭ ሀገራት ጎብኝዎች ገልጸዋል።
“የከተሞች እናት” በኾነችው እድሜ ጠገቧ ጎንደር ከተማ የመስቀል በዓል የሃይማኖት አባቶች፣ የሃይማኖቱ ተከታዮች እና በርካታ እንግዶች በተገኙበት በታላቅ ድምቀት እየተከበረ ነው።
በዚሁ ሃይማኖታዊ በዓል ላይ ከተለያዩ የዓለም ሀገራት የመጡ በርካታ ጎብኝዎችም ታድመዋል።
ከእስራኤል የመጡት አባት እና ልጅ ራህሚን ዛይቪር እና ዴቪድ ራህሚን በዓሉን በጎንደር ከተማ ለመታደም የመስቀል በዓል ከመከበሩ ከአንድ ሳምንት በፊት ወደ ኢትዮጵያ መግባታቸውን ተናግረዋል።
ጎብኝዎቹ በበዓሉ ላይ መታደማቸው ትልቅ ሀሴት እንዳጎናጸፋቸው ገልጸዋል። በርካታ ሕዝብ ነጭ የባሕል ልብስ ለብሶ በኅብረ ዝማሬ እና ሥርዓት ባለው መንገድ በዓሉን ሲያከብር መመልከታቸው በእጅጉ እንዳስገረማቸው ለአሚኮ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያውያን የበርካታ ታሪካዊ እና ባሕላዊ ሃብቶች ባለቤት መኾናቸውን በቆይታቸው መረዳታቸውን የገለጹት እስራኤላውያኑ ይህ ታላቅ ሃብት ተጠብቆ ለወደፊቱ ትውልድ መተላለፍ እንዳለበት መክረዋል።
በተመሳሳይ ከቻይና የመጣው ጎብኝ ጁን ዋንግ የመስቀልን በዓል በጎንደር ከተማ በመታደሙ እና የኢትዮጵያን የማይዳሰስ ሃብት በዐይኑ መመልከት በመቻሉ ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማው ገልጿል።
በዩኔስኮ የማይዳሰስ የዓለም ቅርስ ኾኖ የተመዘገበውን የመስቀል በዓል አከባበር ድባብ የሚያሳዩ ምስሎችን በካሜራዎቻቸው ማስቀረታቸውን የተናገሩት ጎብኝዎቹ ወደ ሀገራቸው ሲመለሱ ለወዳጅ ዘመዶቻቸው ስለ ኢትዮጵያ የሚያስተዋውቁበት እንደሚኾን ጠቁመዋል።
በተጨማሪም በበዓሉ አከባበር በመመሰጣቸው በሚቀጥለው ዓመትም የመስቀልን በዓል ለመታደም ዳግመኛ ወደ ጎንደር ከተማ ለመምጣት ማቀዳቸውን አስታውቀዋል።
#አሚኮ #መስቀል #ኢትዮጵያ🇪🇹
#ጎንደር #መስከረም_17_2019_ዓ_ም
ዘጋቢ፦ ኃይሉ ማሞ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
