
የመስቀል ደመራ በዓል በሰሜን ጎንደር ዞን ደባርቅ ከተማ በተለያዩ ሃይማኖታዊ እና ባሕላዊ ክዋኔዎች ተከብሯል።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የሰሜን ጎንደር ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አሥኪያጅ መልአከ ኀይል አስምሮ ዋካ መስቀል ሰላም እና ድኅነት የታወጀበት የድኅነት በዓል መኾኑን ተናግረዋል።
መስቀል የጥል ግድግዳ የፈረሰበት የይቅርታ እና የአንድነት ምሳሌ መኾኑንም ገልጸዋል።
ሕዝበ ክርስቲያኑ የመስቀሉን ቃል በመከተል በፍቅር፣ በአንድነት እና በመተሳሰብ በዓሉን ማክበር እንደሚገባው አስገንዝበዋል።
የደባርቅ ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ እና የሥራ እና ክህሎት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ልዑል መስፍን የመስቀል በዓል ከሃይማኖታዊ ዕሴቱ በተጨማሪ ዓለም ዓቀፍ ቅርስ እና በርካታ የቱሪዝም ፋይዳ ያለው መኾኑን አንስተዋል።
በዓሉ የመተሳሰብ እና የአብሮነት ነባር ሀገራዊ ዕሴቶች የሚገለጡበት በዓል በመኾኑ ይዘቱን ጠብቆ ማስቀጠል እንደሚገባም ጠቁመዋል።
በበዓሉ ላይ የተገኙት የሃይማኖቱ ተከታዮች በዓሉን በሰላም እና በአንድነት ማክበራቸው ደስታ እንደፈጠረላቸው ገልጸዋል። በዓሉን እርስ በርስ በመረዳዳት እና በመተሳሰብ እያከበሩ እንደሚገኙም ጠቁመዋል።
መስቀል የአንድነት እና የይቅርታ በዓል በመኾኑ ጥላቻን እና ልዩነትን በማስወገድ እና አንድነትን በማጠናከር ማክበር እንደሚገባም መልዕክት አስተላልፈዋል።
#አሚኮ #መስቀል #ኢትዮጵያ🇪🇹
#ደባርቅ #መስከረም_17_2019_ዓ_ም
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
