
የመስቀል ደመራ አበራር ሥነ ሥርዓት በአንዳንድ አካባቢዎች መስከረም 16 ይበራል።
በሰሜኑ የሀገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች ደግሞ መስከረም 17 ላይ ደመራ ይለኮሳል። የጎንደር ነገሥታት ክርስቶስ ንጉሠ ነገሥትነቱን እና ሊቀ ካህንነቱን የገለጸበትን የመስቀል በዓል እያከበሩ መጥተዋል። በዓሉ የከተማይቱ ዋና አደባባይ በነበረው ጃንተከል ዋርካ ወይም በፊት በር ከመስከረም 16 ጀምሮ ሲከበር ቆይቷል።
የክርስቶስ ንጉሠ ነገሥትነቱ የተገለጸበት መስቀል ደመራ የሚደመረው ደግሞ በንጉሠ ነገሥቱ አዛዥነት ነበር። በዚህም አጼ ደመራ ወይንም አጼ መስቀል የሚለውን ስያሜ እንዲያገኝ አድርጎታል። የንጉሠ ነገሥቱ ደመራ እንደማለት ነው።
ይህ ታሪካዊ ሥፍራ በወቅቱ የመስቀል በዓልን ከማክበር ባሻገር አዋጅ ይነገርበታል፤ ሹም ሽር ይፈጸምበታል፤ ለወንጀለኞችም ፍርድ ይሰጥበታል፤ ሊቃውንቱ ጉባኤ ያካሂዱበታል። ከዚህም ባለፈ ለነገሥታቱ ደጅ የሚጠኑበት፣ ባላባቶች ተሰብስበው የተለያዩ ጉዳዮችን የሚመክሩበት ነበር።
በአጠቃላይ ሃይማኖታዊ፣ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ክንውኖች የሚካሄዱበት ሥፍራ ነበር። ከ1966 ዓ.ም ጀምሮ የመስቀል በዓል “መስቀል አደባባይ” እየተባለ ከሚጠራው አካባቢ እንዲከበር ተደርጓል።
በጎንደር በድምቀት ከሚከበሩት በዓላት መስቀል አንዱ ነው። ደመራው የሚበራበት ቀን በ17 ረፋድ ላይ ነው። የመስቀል በዓል ከዋዜማው ጀምሮ የበዓሉ አከባበር በየመንደሩ ባሉ ልጆች በሆያ ሆዬ ጨዋታ እና በሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓት ይደምቃል። እስከ በዓሉ ዕለት ድረስም ይቀጥላል።
የአብነት ተማሪዎችም ከ14 ጀምሮ የቤተክርስቲያን አልባሳትን በመልበስ በየቤቱ እየዙሩ እንኳን አደረሳቹህ ይላሉ። የሰንበት ትምህርት ቤቶች እና ጽዋ ማኅበራት በበዓሉ ቀን የሚቀርቡ መዝሙሮችን፣ ወረብ፣ በገና እና የመሳሰሉ ሃይማኖታዊ ክንውኖች ላይ ቀድመው ይዘጋጃሉ። የአካባቢው ወጣቶች ደግሞ ከበዓሉ በፊት የተጣሉ ካሉ ያስታርቃሉ፤ መስከረም 17 ንጋት ላይ ሊቃነ ጳጳሳት፣ ካህናት፣ ምዕመናን በደመራው ሥፍራ ይገኛሉ። ጸሎት እና ምህላ ይደርሳል፤ ሊቃውንቱ እና የሰንበት ትምህርት ቤቶች ዝማሬ ያቀርባሉ።
ዕለቱን በተመለከተ የወንጌል ትምህርት ተሰጥቶ ሊቀ ጳጳሱ ደመራውን ይባርካሉ። የከተማው ከንቲባ ደግሞ የጥንቱን የንጉሠ ነገሥቱን ሚና ወስደው የተባረከውን ደመራ ከሃይማኖት አባቶች ጋር በመኾን በችቦ ይለኩሳሉ። የተሰበሰበው ሰው ምስጋና ያቀርባል። እናቶችም በእልልታ ያደምቁታል። ደመራው ከተቃጠለ በኋላ የተጸለየበትን እና የተባረከውን አመድ እና ትርኳሽ ሕዝቡ ወደ ቤቱ ይዞ ይሔዳል። በዓሉ ሳይበረዝ በዚህ መንገድ ሃይማኖታዊ ሥርዓቱን ጠብቆ በድምቀት እየተከበረ ዛሬ ላይ ደርሷል።
#ባሕር_ዳር #መስከረም_17_2019_ዓ_ም
በዳግማዊ ተሠራ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
