🔥”አንድ እንጨት ብቻውን አይበራም፤ ጨለማውን የምንገፈው ስንደመር ነው!”

2

 

መስከረም ሲጠባ አበቦች በየሜዳው ፈክተው ልዩ ውበት ይሰጣሉ። መስቀል ሲመጣ ደግሞ የጎንደር ከተማ በእንግዳ ተቀባይነት ባህሏና በመስቀል የደመራ ብርሃን ድምቅ ትላለች።

በጎንደር ከተማ በአንድ ሰፈር ተጎራብተው መኖር ከጀመሩ ከ30 ዓመታት በላይ ያስቆጠሩት ወይዘሮ የኔነሽ ካሰው እና አቶ አያልነህ ክንፉ ይህንን በዓል የሃይማኖት ሥርዓት ብቻ ሳይኾን የዘመናት አብሮነታቸውና የጎረቤታሞች መዋደድ የሚታደስበት ልዩ አጋጣሚ አድርገውታል።

“እኛ ዘንድ መስቀል ማለት መደመር ነው፤ ከሁለት ቀን በፊት ጀምሮ ወጣቶችና አባወራዎች ተሰብስበው የደመራ እንጨት ሲያዘጋጁ እኛ ደግሞ እንጀራና ጠላ እናዘጋጃለን፤ የኛ ደመራ በአንድ ግቢ የሚቆም ሳይሆን የመንደራችን የጋራ ብርሃን ነው!” ይላሉ። በዚህ የፍቅር ድግስ ውስጥ ማንም አይረሳም። የኢኮኖሚ አቅም የሌለው ሰው እንኳ ቢኖር በዓሉን አብሮ በፍቅርና በደስታ እንዲያሳልፍ ይደረጋል።

አቶ አያልነህ ደግሞ “አንድ እንጨት ብቻውን ደመራ አይሆንም፤ ደምቆ አይበራምም፤ ብዙ እንጨት ተሰብስቦ ሲደመር ግን ጨለማውን ይገፍፋል፤ እሳቱም ወደ ላይ ይፈነጥቃል። የኛ ሕይወትና አብሮነትም እንደዚሁ ነው፤ በችግርም በደስታም አብረን ስንቆም ችግራችን ይገፈፋል፤ ፍቅራችን ያበራል፣ ተስፋችንም በብርሃን ይሞላል” በማለት የደመራውን ጥልቅ ምስጢርና ማህበራዊ አብሮነቱን ያስረዳሉ።

መስቀል የዕርቅና የሠላም ማህተም ነውና ያለ ይቅርታ በዓሉ አይደምቅም። ባለፈው ዓመት በመካከላቸው ጥቂት አለመግባባቶች ቢኖሩ እንኳ እንጨት ከመሰብሰቡና ደመራው ከመለኮሱ ከሁለት ሦስት ቀን በፊት ሽማግሌዎች ሰብሰብ ብለው እርቅ ያወርዳሉ።

ወይዘሮ የኔነሽና አቶ አያልነህ በጎረቤት ፍቅርና በአብሮነት የሚያሳዩን እውነት ቢኖር የመስቀል በዓል የሃይማኖታዊ ክንዋኔነቱን ያህል የሕዝባችን የይቅርታ፣ የዕርቅና የዘመናት ሠላም ማህተም መሆኑን ነው።

#አሚኮ #መስቀል #Ethiopian ✝️🇪🇹

#ባሕር_ዳር #መስከረም_17_2019_ዓ_ም

✍️ ዘጋቢ፦ ቴዎድሮስ ደሴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous article✝️ የአጼ ዘርዓ ያዕቆብ ራዕይ እና የኢየሱስ ክርስቶስ ግማደ መስቀል በግሸን አምባ ማረፍ !