
የመስቀል በዓል ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበት ቅዱስ መስቀል ተቀብሮ ለዘመናት ከቆየ በኋላ በንግሥት ዕሌኒ አማካኝነት መገኘቱን በማስታወስ የሚከበር በዓል ነው።
የርእሰ አድባራት ወገዳማት መርጡለ ማርያም ገዳም አሥተዳዳሪ ርእሰ ርዑሳን አባ ብርሃነ መስቀል አንዳርጌ ኢየሱስ ክርስቶስ ከተሰቀለ በኋላ ቅዱሱን መስቀል በመዳሰስ በርካታ ሕሙማን ይፈወሱ እና ድንቅ ተዓምራት ይታዩበት እንደነበር ገልጸዋል። ይህንን የተመለከቱት አይሁድ በቅንዓት ተነሳስተው የመስቀሉን ዝና ለማጥፋት ጥልቀት ባለው ጉድጓድ ተቆፎሮ እንዲቀበር አደረጉት ብለዋል። ከዚያም የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ሁሉ የቤታቸውን ቆሻሻ እና ጥራጊ መስቀሉ ባለበት ቦታ ላይ እንዲጥሉ አዘዙ፤ በዚህም የተነሳ መስቀሉ የተቀበረበት ሥፍራ ለበርካታ ዓመታት በቆሻሻ ተራራ ተሸፍኖ ኖረ ነው ያሉት።
በኋላም የሮማው ንጉሥ ቆስጠንጢኖስ እናት የነበሩት ንግሥት ዕሌኒ የጠፋውን ቅዱስ መስቀል ፈልገው ለማውጣት ወደ ኢየሩሳሌም እንደተጓዙ አስገንዝበዋል። ይሁን እንጂ መስቀሉ የተቀበረበትን ትክክለኛ ቦታ ለማወቅ ተቸግረው ነበር ይላሉ። ኪራኮስ የተባለ አረጋዊ ሰውም የእንጨት ክምር እንዲደመር እና እጣን እንዲጨመርበት ከዚያም በእሳት እንዲለኮስ ጠቆሟት ነው ያሉት።
በዚህም ምክንያት የእሳቱ ጭስ ወደ ሰማይ ወጥቶ ቁልቁል በመመለስ መስቀሉ የተቀበረበትን ተራራ እንዳመላከታቸው ነው የተናገሩት። ያንን ታሪክ ለመዘከር በየዓመቱ መስከረም ወር ላይ መስቀል በዓል ይከበራል ብለዋል።
ግማደ መስቀሉ ወደ ሀገር ውስጥ መግባቱ ሌላኛው ታራክ ነው የሚሉት አሥተዳዳሪው የኢትዮጵያ ነገሥታት በተለይም በአጼ ዳዊት የተጀመረው በልጃቸው አጼ ዘርዓ ያዕቆብ መግባቱን ገልጸዋል። ግማደ መስቀሉ ወደ ኢትዮጵያ ከገባ በኋላ አጼ ዘርዓ ያዕቆብ “መስቀሌን በመስቀለኛ ቅርጽ ባለው ቦታ አስቀምጥ” የሚል መለኮታዊ ራዕይ በተደጋጋሚ በማየታቸው ፍለጋ ካደረጉ በኋላ በመስቀል ቅርጽ በተፈጥሮ የተሠራውን ግሼ አምባ ወይም ግሸን ማርያምን በመምረጥ መስከረም 21 ቀን 1446 ዓ.ም እንዲያርፍ ተደርጓል ነው ያሉት።
መስቀሉ የሰላም ምልክት እና የሰው ልጅ ነጻ የወጣበት እንደኾነም አንስተዋል።
#አሚኮ #መስቀል #Ethiopian ✝️🇪🇹
#ባሕር_ዳር #መስከረም_17_2019_ዓ_ም
✍️ በሥራውድንቅ ደሳለው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
