🌼 “የት እንደከረመች አትጠየቅም፤ ወዴት እንደምትሰወርም አይታወቅም”🕊️

12

 

ዘፋኙ “የመስቀል ወፍ እና አንቺ ልጅ ያው ናችሁ፤
በዓመት አንዴ ብቻ ብቅ ትላላችሁ” በማለት ያዜመው የመስቀል ወፍ በመስከረም ያውም በመስቀል ሰሞን ተናፋቂ መኾኗን ለመግለጽ ነው።

የመስቀል ወፍ ከከባድ የደመና መጋረጃ እና ከጨለማው የክረምት ወቅት ፈልቃ የምትወጣ አካላዊ ክንፍ ያላት ተራ ምድራዊት ፍጡር ብቻ አይደለችም። ከማይታየው የዓለማት ጠርዝ ተገንጥላ ወደ እኛ የምትመጣ የዘላለም ቅንጣት ጭምር እንጂ።

ሰማይ እና ምድር የሚገናኙበትን ያን ጠባብ የሽግግር ድልድይ አቋርጣ ስትመጣ የጽንፈ ዓለሙን ጥልቅ እስትንፋስ እና ከዘመናት በፊት የተሰወረውን የፍጥረት ምስጢር ታካፍላለች።

የክንፏ ድምፅ የሌለው ርግብግቢት ከቃላት በላይ የኾነውን የተፈጥሮን ጸጥተኛ የልብ ምት ወደ ሰዎች ነፍስ ያስተላልፋል። በቀለማት ያሸበረቀው መልኳ እና በውስጡ የተሸሸገው ብርሃን የተራ ፀሐይ ነጸብራቅ ብቻ ሳይኾን ከሰው ልጅ የነፍስ ጓዳ ጋር የሚያወራ ረቂቅ ቋንቋ ነው።

የት እንደከረመች አትጠየቅም፤ ወዴት እንደምትሰወርም አይታወቅም። መከሰቷ ራሱ በጊዜ እና በቦታ መካከል የተፈጠረ ቅጽበታዊ ስንጥቅ ይመስላል፤ እርሷ ስትገለጥ ጊዜው ደስ ይላል፣ የሜድርም ውበት የበለጠ ያምራል። ያረጀው የምድር ገጽ ታድሶ በአዲስ መንፈስ ይወለዳል።

መሬት በቢጫው የአደይ አበባ ስትከበብ እርሷ ከሰማይ ኾና የዚህን ወርቃማ ምንጣፍ ጸጥተኛ ኹነት ትታደማለች። እያንዳንዱ የክንፏ እንቅስቃሴ የሰማዩን ዝናብ ወደ ተስፋ ጠልነት የሚቀይረው ይመስላል።

በብርሃን እና በጨለማ፣ በሐዘን እና በደስታ፣ በሞት እና በትንሣኤ መካከል ያለውን ቀጭን ክር በማሰር የሕላዌን ሚዛን ትጠብቃለች።

መጥፋቷም እንደ መምጣቷ እንቆቅልሽ ነው። ቦታን እና ጊዜን ተሻግራ፣ ምድራዊውን የሐዘን ካባ ገፈፍ አድርጋ፣ አላፊነትን እና ዘላለማዊነትን በአንድነት አዋህዳ በጸጥታ ትሰወራለች።

እንደ ኢትዮጵያ የብዝኃ ሕይወት ኢንስቲትዩት ምስክርነት የመስቀል ወፍ ከ10 በላይ ዝርያዎች አሏት።

አዕዋፋትን በቅርበት የሚያጠኑት ይልማ ደሳለኝ በበኩላቸው የመስቀል ወፎች ዘወትር አብረውን የሚኖሩ ናቸው ይላሉ። ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ በመስቀል ሰሞን በብዛት የሚታዩት የሚመገቡት ሰብል ስለሚደርስ እና የመራቢያ ወቅታቸው በመኾኑ እንደኾነ አስረድተዋል።

የመስቀል ወፍ በዓይናችን አግኝተን ልናጣት የምንችል ነገር ግን በነፍስ ጓዳ ውስጥ የማይደበዝዝ የብርሃን አሻራ ትታ የምትጠፋ፣ ጠፍታም የማትቀር ረቂቅ ፍጥረት ናት።

#አሚኮ #መስቀል #Ethiopian ✝️🇪🇹

#ባሕር_ዳር #መስከረም_17_2019_ዓ_ም

✍️ በስማቸው አጥናፍ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleለጽኑ ኅብረ ብሔራዊ አንድነት የማይናወጥ መሠረት የጣለች ባለ ራዕይ ሀገር- ኢትዮጵያ🇪🇹
Next article✝️ የአጼ ዘርዓ ያዕቆብ ራዕይ እና የኢየሱስ ክርስቶስ ግማደ መስቀል በግሸን አምባ ማረፍ !