🔥 የደመራው ፍም እና የሰላም ብርሃን🕊️

7

 

ኢትዮጵያ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በተለያዩ አካባቢዎች በቀጠሉ ግጭቶች ከፍተኛ የሰላም መታወክ አጋጥሟታል። በዚህ የፈተና ወቅት እንደ መስቀል በዓል ያሉ ሀገራዊ እና ሃይማኖታዊ የአደባባይ በዓላት ከበዓልነት ባለፈ ለሰላም ግንባታ ያላቸው አስተዋጽኦ እጅግ የጎላ ነው።

በዩኔስኮ (UNESCO) የማይዳሰስ ባሕላዊ ቅርስ ኾኖ የተመዘገበው ይኸው በዓል በውስጡ ጥልቅ የኾኑ የይቅርታ፣ የእርቅ እና የአንድነት ትርጉሞችን አዝሏል።

እንደ ሃይማኖቱ አባቶች አስተምህሮ መሠረት የደመራው መለኮስ በታሪካዊ አመጣጡ የጠፋውን መስቀል ለማግኘት የተደረገውን ጥረት እና ጭሱን ተከትሎ የተገኘውን ብርሃን ያመለክታል። ይህ መንፈሳዊ ክዋኔ በማኅበራዊ አውድም ቂምን፣ ጥላቻን እና መከፋፈልን በእሳት አቃጥሎ አዲስ ብርሃንን እና ተስፋን የመቀበል ተምሳሌት ነው።

የበዓሉን እሴት በማንሳት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) የመስቀል በዓል ቤተሰብን እና ማኅበረሰብን የሚያስተሳስር የመደመር ተምሳሌት መኾኑን ገልጸዋል። የደመራውን እንጨት መሰባሰብ ለአብነት በመጥቀስም ዜጎች ይህንን የአንድነት መንፈስ በመላበስ የኢትዮጵያን ጸጋዎች በማስተሳሰር ታላቅ ሀገራዊ አቅም ለመፍጠር በጋራ እንዲተጉ ጥሪ አቅርበዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያነሱት ይህ የማኅበረሰብ ትስስር በተግባር ሲታይ ባሕላዊ እና ሃይማኖታዊ በዓላት የሰዎችን ሥነ-ልቦና ወደ አዎንታዊ አቅጣጫ በማምጣት ረገድ ትልቅ አቅም አላቸው። የመስቀል በዓል ሰዎች ተሰባስበው አንድ ላይ ደመራ የሚለኩሱበት፣ አብረው የሚመገቡበት እና ጠብን የሚረሱበት ልዩ አጋጣሚ ነው።

በተለያዩ ጊዜያት በማኅበረሰቦች መካከል ለሚፈጠሩ አለመግባባቶች የሀገር ሽማግሌዎች እና የሃይማኖት አባቶች በዓላትን መሠረት አድርገው የሚያወርዷቸው እርቆች ለዚህ ሕያው ማሳያ ናቸው። የመስቀል በዓል የሰላም ትርክትን በተጨባጭ መሬት ላይ ለማውረድ እንደ አንድ ትልቅ ማኅበራዊ ካፒታል ሊያገለግል ይችላል።

አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ላለው የፖለቲካ እና የትጥቅ ግጭት ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት ከጦር መሳሪያ ይልቅ ብሔራዊ መግባባት ወሳኝ ነው። ይህንን በሕዝቡ ዘንድ ያለውን የይቅርታ እና የአብሮነት መንፈስ ወደ ፖለቲካው መድረክ እና ወደ ተፋለሙት ኀይሎች ልቦና ማሸጋገር ያስፈልጋል።

ጥላቻን እና መከፋፈልን በማስወገድ የሰላምን ብርሃን መከተል የሁሉንም ኢትዮጵያዊ የጋራ ኀላፊነት ይጠይቃል።

የእውነተኛ ሰላም ጅማሮ ከልብ በሚመነጭ ይቅርታ እና መቻቻል ላይ የሚመሰረት በመኾኑ በዓሉን የብሔራዊ መግባባት እና የልብ መታደስ መነሻ ማድረግ ይገባል።

#አሚኮ #Meskel #Ethiopian ✝️🇪🇹

#ባሕር_ዳር #መስከረም_17_2019_ዓ_ም

✍️ በስማቸው አጥናፍ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleከመስቀሉ የምንማረው ታላቅ ቁምነገር የሰላም መሣሪያ መኾንን ነው።
Next articleለጽኑ ኅብረ ብሔራዊ አንድነት የማይናወጥ መሠረት የጣለች ባለ ራዕይ ሀገር- ኢትዮጵያ🇪🇹