ከመስቀሉ የምንማረው ታላቅ ቁምነገር የሰላም መሣሪያ መኾንን ነው።

1

 

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ዘንድ በየዓመቱ በተለየ ድምቀት ከሚከበሩ ሃይማኖታዊ በዓላት መካከል መስቀል አንዱ ነው።

ይህ የመስቀል በዓል በሃይማኖቱ ተከታዮች ዘንድ ትርጉም ተሰጥቶት ይከበራል። የፍቅር፣ የሰላም፣ የድል፣ የይቅርታ እና ከሁሉም በላይ ደግሞ የእውነት ማኅተም ተደርጎም ይታያል።

በየዓመቱ መስከረም 17 የሚከበረው የመስቀል በዓል የሃይማኖቱ ተከታዮች እውነት በዓለማዊ ኃያላን ብትቀበር እና ለዘመናት የቆሻሻ ክምር ቢጫንባትም ጊዜዋን ጠብቃ እንደ ንጋት ፀሐይ መውጣቷ አይቀሬ መኾኑን የሚማሩበት ትልቅ መንፈሳዊ መዝገብ ነው።

ከአሚኮ ጋር ቆይታ ያደረጉት በባሕር ዳር ሀገረ ስብከት የመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ስብከተ ወንጌል ክፍል ኃላፊ መጋቢ ሐዲስ ሰምዓኮነ ያየህ ይራድ የመስቀልን በዓል አከባበር ታሪካዊ መሠረት ሲያብራሩ በቅድሚያ የመስቀሉ ባለቤት ማነው የሚለውን ማየት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

ኢየሱስ ክርስቶስ ወደዚህ ዓለም መጥቶ ካስተማረ በኋላ በዕለተ ዓርብ በቀራኒዮ ዓደባባይ እንደተሰቀለ እና በሥልጣኑ ከተነሳ በኋላ መስቀሉ በደሙ ከብሮ ድንቅ ተዓምራትን ማድረግ እንደጀመረ ያስረዳሉ።

ታዲያ በዚህ የተበሳጩ አይሁዳዊያንም መስቀሉን ቀብረውታል ብለዋል። ከቀበሩት በኋላም ሕዝቡ የቤቱን ቆሻሻ በሙሉ መስቀሉ ላይ እንዲጥል እና አዋጁን ያልፈጸመ ንብረቱ እንደሚወረስ ማወጃቸውን ይናገራሉ። ለ300 ዓመታት መስቀሉ ተቀብሮ ቆሻሻ ሲጣልበት መኖሩን እና የተጣለው ቆሻሻ ተራራ መሥራቱን ነው የተናገሩት።

ነገር ግን መስቀሉ በእግዚአብሔር ጥበብ ተጠብቆ ምስጥ እንዳይበላው፣ እንዳይነቅዝ እና እንዳይበሰብስ ተደርጎ ስለመቆየቱ ነው ያነሱት።

ከዚያም ንግሥት ዕሌኒ የክርስቶስን መስቀል ከተቀበረበት አውጥታ በክብር ለመጠበቅ እና ቦታውን ለማደስ በገባችው ቃልኪዳን መሠረት ወደ ኢየሩሳሌም መጓዟን ተናግረዋል።

መስቀሉ ያለበትን ስፍራ የሚያውቅ በጠፋበት በዚያ ወቅት ኪራኮስ የተባሉ አረጋዊ በጠቆሟት አቅጣጫ መሠረት ደመራ አስደምራ ዕጣን ስታጨስ የዕጣኑ ጭስ መስቀሉ ወደተቀበረበት ቦታ እንዳመላከታት ሃይማኖታዊ አስተምህሮው እንደሚነግረን ጠቅሰዋል። በዚህም መሠረት ቁፋሮ ተጀምሮ ክቡር መስቀሉ ከምድር ሊወጣ ችሏል ነው ያሉት።

ይህ የታሪክ ሂደት መስቀሉ የእውነት ምልክት መኾኑን እንደሚያሳይ የሚናገሩት መጋቢ ሐዲስ ሰምዓኮነ መስቀሉ እውነተኛ እንደኾነ እና ተሸሽጎ የነበረ ቢኾንም ከዘመናት በኋላ መውጣቱ እውነት በሐሰት ተደብቆ እንደማይቀር ማረጋገጫ ይኾናል ብለዋል።

በመስቀሉ አማካኝነት ችግር እና ጥል የተወገደ በመኾኑ ምዕመናን የመስቀሉን የእውነት፣ የድል አድራጊነት፣ የይቅርታ፣ የመቻቻል እና የጽናት እሴቶች በዕለት ከዕለት ሕይወታቸው ሊተረጉሟቸው እንደሚገባ ነው መምህሩ ያሳሰቡት።

የሰላም መሣሪያ መኾንን ሌላው ከመስቀሉ የምንማረው ታላቅ ቁም ነገር ነውም ብለዋል። ነቢዩ ኢሳያስ ክርስቶስን የሰላም አለቃ ብሎ እንደጠራው ሁሉ የሰላም ማደሪያ መኾን ምዕመናን በሕይወታቸው ሊተረጉሙት የሚገባ የመጀመሪያው ተግባር መኾኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።

መጋቢ ሐዲስ ሰምዓኮነ ያየህይራድ መልዕክታቸውን ሲያጠቃልሉ ክርስቶስ የተሰቀለው ያለ ምንም አድልኦ ለሁሉም የሰው ልጆች በመኾኑ ምዕመናንም ፍቅርን ለሁሉም ሰው ያለ አድልኦ መስጠት አለባቸው ብለዋል።

እንኳን ለብርሃነ መስቀሉ አደረሳችሁ ✝️

#አሚኮ #Meskel #Ethiopian ✝️🇪🇹

#ባሕር_ዳር #መስከረም_17_2019_ዓ_ም

✍️ ዘጋቢ፦ አድኖ ማርቆስ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous article“ከ1 ነጥብ 6 ሚሊዮን በላይ የውጭ ዜጎች ኢትዮጵያን ጉብኝተዋል” የቱሪዝም ሚኒስቴር
Next article🔥 የደመራው ፍም እና የሰላም ብርሃን🕊️