“ከ1 ነጥብ 6 ሚሊዮን በላይ የውጭ ዜጎች ኢትዮጵያን ጉብኝተዋል” የቱሪዝም ሚኒስቴር

6

‎
‎በጎንደር ከተማ ዓለም አቀፍ የቱሪዝም ቀን አስመልክቶ የቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ በተገኙበት የቱሪዝም ሥፍራዎች የጉብኝት መርሐግብር ተካሂዷል።
‎
በመርሐግብሩ ላይ ‎ባለፈው ዓመት ከ 1 ነጥብ 6 ሚሊዮን በላይ የውጭ ዜጎች ኢትዮጵያን ጎብኝተዋል ያሉት የቱሪዝም ሚኒስትሯ ሰላማዊት ካሳ መንግሥት ለዘርፉ ትኩረት ሰጥቶ በመሥራቱ 5 ቢሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱን አንስተዋል።
‎
‎አሠራርን በማዘመን የሀገር ውስጥ ቱሪዝምን ማበረታታት እንደሚገባም አንስተዋል። ክልሎች ለዘርፉ ትኩረት ሰጥተው እንዲሠሩ መደረጉንም አመላክተዋል።
‎
‎ባለፈው ዓመት ከ800 በላይ የቱሪስት መዳረሻዎች ልየታ እንደተደረገም ጠቁመዋል።
‎
‎ጎብኝዎች ደኅንነታቸው ተጠብቆ የቆይታ ጊዜያቸውን በጥሩ ሁኔታ እንዲያሳልፉ እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል።
‎
‎የቱሪዝም ቀን በጎንደር መከበሩ ትልቅ ጠቀሜታ እንዳለው ያነሱት የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው ጎንደር የበርካታ ታሪካዊ ቅርሶች መገኛ ናት ብለዋል።
‎
‎የፋሲል ቤተመንግሥት ለቱሪስቶች ቀዳሚ መዳረሻ መኾኑንም ገልጸዋል። በርካታ ቱሪስቶች ወደ ከተማዋ መምጣታቸውንም አንስተዋል።
‎
‎ለቱሪዝም ምቹ ሁኔታን በመፍጠር ከዘርፉ የሚገኝን ተጠቃሚነት ከፍ ለማድረግ ይሠራልም ነው ያሉት።
‎
‎በጉብኝቱ አሚኮ ያገኛቸው ከተለያዩ ክልሎች የመጡ የሥራ ኀላፊዎች ቅርሶች ታሪካዊ ይዘታቸውን ጠብቀው መታደሳቸው ይበልጥ የቱሪስት ፍሰትን የሚጨምር ነውም ብለዋል።

#አሚኮ #መስቀል #ኢትዮጵያ🇪🇹

#ጎንደር #መስከረም_17_2019_ዓ_ም

ዘጋቢ፦ አምሳሉ አደራጀው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous article“እንደ ደመራው በአንድነት የፍቅር ሸማ ለብሰን አንድ እንሁን”
Next articleከመስቀሉ የምንማረው ታላቅ ቁምነገር የሰላም መሣሪያ መኾንን ነው።