
ደመራ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በታላቅ መንፈሳዊ እና ባሕላዊ ክዋኔ የሚከበር በዓል ነው። በሃይማኖታዊ አስተምህሮው መሠረት ደመራ ቅዱስ መስቀሉ የተገኘበትን የፍለጋ ምስጢር ይዘከርበታል።
የደመራ በዓል ልዩ ምስጢር ያለው፣ ረቂቅ ሥርዓተ አምልኮ የሚንጸባረቅበት እና ልዩ ልዩ መንፈሳዊ ክዋኔዎች የሚከወኑበት ሃይማኖታዊ በዓል ነው።
✝️በዓሉ እንዴት ይከበራል?
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስትያን በባሕር ዳር ሀገረ ስብከት በገዳመ ዮርዳኖስ መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ቤተ ክርስቲያን መምህር እና የስብከተ ወንጌል ኀላፊ ለቤዛ ጥላሁን እንዳስረዱት በደመራ በዓል በርካታ ክዋኔዎች ይከናወናሉ።
በዕለቱ ካህናት፣ ዲያቆናት፣ መዘምራን እና አማኞች ወደ ደመራው አደባባይ ያመራሉ። ሁሉም የመስቀል አይነቶች ከየአድባራት ይወጣሉ። ከአማኞች የተሠበሠበው እንጨት እና ችቦ በተዘጋጀው አደባባይ (የደመራ ቦታ) ላይ ይደመራል።
ሁሉም ካህናት የተፈቀደላቸውን የልብሰ ተክህኖ ይለብሳሉ። ሊቃውንቱ ካባ ይደርባሉ። መቋሚያቸውን ይይዛሉ። ወረብ፣ ጸሎት፣ መዝሙር፣ የትምህርተ ወንጌል አገልግሎቶች ይከናወናሉ። የጸሎት እና የቡራኬ ሥርዓት ይከናወናል። የሰንበት ትምህርት ቤት መዘምራንም በዓሉን የሚያንጸባርቁ ያሬዳዊ ዝማሬዎችን ያቀርባሉ።
ወንጌል ተነቦ፣ ቡራኬ እና የዕለቱ ትምህርተ ወንጌል ከተሰጠ በኋላ በሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ መሪነት ካህናት ደመራውን ሦሥት ጊዜ ይዞራሉ። በአራቱም አቅጣጫ ይባረካል። ቀጥሎም በሊቀ ጳጳሱ አማካኝነት ደመራው ተለኩሶ እንዲቃጠል ይደረጋል።
እንጨቱ በሚነድበት ወቅት የሚወጣው እሳት እና ጭስ ንግሥት ዕሌኒ መስቀሉን ያገኘችበትን የጭስ አቅጣጫ የሚያስታውስ በመኾኑ አማኞች በታላቅ እልልታ፣ ዝማሬ እና ሆታ ያከብሩታል።
የደመራ በዓል የፍቅር እና የአንድነት መገለጫ ነው። ደመራው ለመስቀሉ መገኘት ምክንያት እንደኾነ ሁሉ፣ የመስቀሉ ፍቅር ደግሞ አማኞችን በአንድነት እንዲሠባሠቡ ምክንያት ኾኗል።
✝️ደመራ ምን ያስተምራል?
መምህር ለቤዛ እንዳስረዱት ደመራ አንድነትን ያስተምራል። አንድነት ደግሞ የፍቅር ውጤት ነው። ደመራው ከተለያየ ቦታ ከተሠባሠበ ከተለያየ እንጨት እንደሚደመር ሁሉ የተለያየ ግብር ያለው ሰው ሁሉ በሰብዓዊነት ጥላ ስር አንድ ሊኾን ይገባል ብለዋል።
ደመራው እንደገበያ ነው የሚሉት መምህሩ በገበያ የማይተዋወቁት ሰዎች ተገበያይተው እንደሚመለሱት ሁሉ በደመራም አማኞች በአንድነት ተሠባሥበው ፍቅርን የሚገበዩበት ነው ብለዋል።
በደመራው የተሠበሠበው እንጨት መስቀሉን ለማመልከት እንደነደደ ሁሉ የተቸገረን ለመርዳት ከራስ አልፎ ለሌሎች መኖርን፣ ዋጋ መክፈልን እና መተሳሰብን እንደሚያስተምር አስገንዝበዋል።
“ኢትዮጵያ የፍቅር ሀገር፣ ኢትዮጵያውያንም የፍቅር ሰዎች ነን እና እንደ ደመራው በአንድነት የፍቅር ሸማ ለብሰን አንድ ልንኾን ይገባል” ብለዋል።
#አሚኮ #Meskel #Demera #Ethiopia 🇪🇹
#ባሕር_ዳር #መስከረም_17_2019_ዓ_ም
✍️በአሰፋ ልጥገበው
- የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
