
የመስቀል ደመራ በዓል በባሕር ዳር ከተማ በልዩ ልዩ ሃይማኖታዊ ክንዋኔዎች እየተከበረ ነው። በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የባሕር ዳር እና የሰሜን ጎጃም አሕጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ብጹዕ አቡነ አብርሐም መልዕክት አስተላልፈዋል።
ለ300 ዓመታት ተቀብሮ የነበረው መስቀል በንግሥት ዕሌኒ ትጋት እና በአረጋዊው ኪራኮስ ጥበባዊ ምክር መሠረት መገኘቱን በማውሳት የበዓሉን ታላቅነት አስገንዝበዋል።
የመስቀሉን የሰላም እና የፍቅር ትርጓሜ ከአሁኑ የሀገራችን ነባራዊ ሁኔታ ጋር በማስተሳሰርም ኢትዮጵያውያን ከልብ የመነጨ ሰላም እና ፍቅር ሊኖራቸው እንደሚገባም አሳስበዋል።
“ሰላም እና ፍቅር” የሚሉት ቃላት በብዙዎች አንደበት ቢደጋገሙም ከልብ የመነጩ ባለመኾናቸው በተግባር ማየት ግን እየቀነሰ መኾኑን ተናግረዋል።
አንጀቱ ያላዘነ ሊያነባ እንደማይችል ሁሉ እውነተኛ ሰላምም ከውስጥ ካልፈለቀ ለሀገር መረጋጋትን ሊያመጣ እንደማይችል አስረድተዋል።
በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ እየታየ ያለው ግጭት መከባበር በመጥፋቱ እና የሃይማኖት አባቶች እንዲሁም የሀገር ሽማግሌዎች የነበራቸው አስታራቂነት እና የመገሰጽ ሥልጣን በመዳከሙ የመጣ ነው ብለዋል።
የሰላም እጦቱ ኢትዮጵያ ያላትን ታላቅ ጸጋ በመጠቀም የውጭ ቱሪስቶች እንደ ጎርፍ መጥተው ታሪኳን ሊያጠኑ የሚችሉበትን ሰፊ ዕድል እንዳሳጣትም አንስተዋል።
ዜጎች ከጥላቻ ነፃ በመኾን እውነተኛ ፍቅርን በተግባር እንዲሰብኩ እና ሰላምን እንዲያመጡ አባታዊ ጥሪያቸውንም አቅርበዋል።
#አሚኮ #መስቀል #ኢትዮጵያ🇪🇹
#ባሕር_ዳር #መስከረም_16_2019_ዓ_ም
✍️ በስማቸው አጥናፍ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
