
የመስቀል ደመራ በዓል በአዲስ አበባ ከተማ በድምቀት እየተከበረ ነው።
በበዓሉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ፣ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት፤ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ ማርቶማ ማቴዎስ ፫ኛ የሕንድ ማላንካራ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ጨምሮ የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።
በበዓሉ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የባሕል እና ስፖርት ሚኒስትሯ ሸዊት ሻንካ የመስቀል በዓል የሃይማኖታዊ ሥርዓት መገለጫ ብቻ ሳይኾን የኢትዮጵያውያን የተከበረ እና በደማቅ ታሪክ የተጻፈ ማንነት የምናሳይበት ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ የሥልጣኔ መሠረት የኾኑ ባሕላዊ፣ ታሪካዊ እና ሃይማኖታዊ የዓደባባይ በዓላት፣ እሴቶች እና ሀገር በቀል ዕውቀቶች አብሮነትን የሚያጠናክሩ መኾናቸውን ገልጸዋል። የሕዝብን ማኅበራዊ ትስስር እና ሀገራዊ አንድነትን የሚያጠናክሩ መኾኑንም አንስተዋል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የታሪክ ባለቤት እና የጽናት ተምሳሌት ናት ያሉት ሚኒስትሯ ለዚህ አብነቱ በሺዎች ዘመናትን የተሻገረውን የመስቀል በዓል ጠብቃ ለዓለም ማበርከቷ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት ፈተናዎችን በአይበገሬነት እና በድል እያለፈች በበርካታ ዘርፎች አስደናቂ የልማት ስኬቶችን እያስመዘገበች መኾኗንም አንስተዋል። ስኬቶቹ በብርቱ ሥራ እና በሕዝብ ትብብር የመጡ መኾናቸውን ነው የተናገሩት።
ከትናንት ወረቶች የዛሬ ስኬቶችን ጨምረን የበለጸገች ሀገር ለመገንባት፤ የኢትዮጵያን ከፍታ ለማረጋገጥ እና የባሕር ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ ኢትዮጵያውያን እንደ ደመራ ችቦ እጅ ለእጅ ተያይዘን የምንነሳበት ጊዜ ነው ብለዋል።
የመስቀልን በዓል ጠብቀው ላቆዩት ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል። በዓሉ የሰላም እና የፍቅር እንዲኾንም ተመኝተዋል።
#አሚኮ #መስቀል #ኢትዮጵያ🇪🇹
#ባሕር_ዳር #መስከረም_16_2019_ዓ_ም
✍️ በታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
