
ለዘመናት ባሕላዊ እና ሃይማኖታዊ እሴቱን የጠበቀው የመስቀል ደመራ በዓል በደብረ ማርቆስ ከተማ በንጉሥ ተክለ ሃይማኖት ዓደባባይ በታላቅ ድምቀት ተከብሯል።
በበዓሉ አከባበር ሥነ ሥርዓት ላይ የምሥራቅ ጎጃም፣ አዊ እና መተከል አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ብጹዕ አቡነ ቶማስ፣ የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ተሾመ ዋለ፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የከተማዋ አድባራት እና ገዳማት ካህናት፣ መምህራን፣ የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች እና በርካታ ምዕመናን ተገኝተዋል።
በበዓሉ መልዕክት ያስተላለፉት የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ተሾመ ዋለ ንግሥት እሌኒ መስቀሉን ለማግኘት ከከፈለችው መስዋዕትነት እና ካሳየችው ጽናት በመማር በአንድነት እና በአብሮነት ለሀገር ዕድገት እና ሰላም መትጋት ይገባናል ብለዋል።
ከመስቀል በዓል ፍቅርን፣ መተሳሰብን እና አንድነትን በመላበስ ለበጎ ሥራ ሁሉ በጋራ መቆም እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
የምሥራቅ ጎጃም፣ አዊ እና መተከል አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ብጹዕ አቡነ ቶማስ የመስቀሉ መገለጥ ለዓለም ደኅንነትን፣ ፍቅርን እና ሰላምን ይዞ የመጣ መኾኑን ገልጸዋል።
በዓሉን ስናከብር ሰላምን፣ አንድነትን እና መተሳሰብን ገንዘብ በማድረግ ሊኾን እንደሚገባ አስገንዝበዋል። እያንዳንዱ ዜጋ ለሀገር ሰላም ቀናኢ እና ተባባሪ መኾን እንዳለበት አባታዊ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
#አሚኮ #የመስቀል_ደመራ_በዓል #አማራ_ክልል #ኢትዮጵያ
#ደብረ_ማርቆስ #መስከረም_16_2019_ዓ_ም
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
