“ወቅቱ የእርቅ መንፈስን የሚጠይቅ በመኾኑ ያለፈውን በይቅርታ አልፎ አንድነትን ማጠናከር ይገባል” አቶ ጎሹ እንዳላማው

8

 

የመስቀል ደመራ በዓል በባሕር ዳር ከተማ በድምቀት እየተከበረ ነው።

በበዓሉ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው በዓሉ ሃይማኖታዊ፣ ማኅበራዊ እና ባሕላዊ እሴቱን ጠብቆ ለትውልድ ሲተላለፍ የቆየ የዓለም ቅርስ ነው ብለዋል። የኢትዮጵያውያን የጋራ ኩራት እና የአንድነት መገለጫ መኾኑንም ገልጸዋል።

ንግሥት ዕሌኒ የጠፋውን መስቀል በጭስ እና በቁፋሮ ጥረት እንዳገኘችው ሁሉ የደመራው መብራትም ጨለማ እንደሚገፈፍ እና ብርሃን እንደሚገለጥ የሚያሳይ ተምሳሌት ነው ብለዋል። ይህ ክዋኔ ማኅበረሰቡ በጊዜያዊ ችግሮች እና ፈተናዎች ፊት የተጋረጠበትን ጨለማ በውይይት፣ በንግግር፣ በጥበብ መፍታት እና ማለፍ እንደሚችል የሚያስተምር እንደኾነ ነው የገለጹት።

ከየአቅጣጫው የተሠበሠቡ እንጨቶች ተደምረው አንድ ደመራ እንደሚኾኑ ሁሉ ሰዎችም በበዓሉ ተሠብሥበው ይቅርታ የሚጠያየቁበት እና ኅብረት የሚጠናከርበት አጋጣሚ ነው ብለዋል። ወቅቱ የእርቅ መንፈስን የሚጠይቅ በመኾኑ ያለፈውን በይቅርታ አልፎ አንድነትን ማጠናከር እንደሚገባም ተናግረዋል።

በተለይም በአሁኑ ወቅት በባሕር ዳር ከተማ ሰላም በመረጋገጡ የጎብኝዎች ዐይን ማረፊያ እየኾነች እንደኾነ አንስተዋል። በመኾኑም ነዋሪዎች የከተማዋን ሰላም እና ልማት ለሌሎች በማብሰር፣ ሰላምን የማይፈልጉ አካላትን ደግሞ በአንድነት በመመከት እና የአካባቢያቸውን ደኅንነት በመጠበቅ ኀላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

መከባበርን፣ እውነተኛ ወንድማማችነትን እና ታላላቆችን የማክበር ባሕል በጥበብ እና በትዕግሥት መልሶ ማግኘት ወቅቱ የሚጠይቀው አንገብጋቢ ጉዳይ መኾኑንም ገልጸዋል።

#አሚኮ #መስቀል #ኢትዮጵያ🇪🇹

#ባሕር_ዳር #መስከረም_16_2019_ዓ_ም

✍️ በስማቸው አጥናፍ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous article‎ፍትሕን በማስፈን በክልል ደረጃ አንደኛ ደረጃን ያገኘው የሰሜን ሸዋ ዞን ፍትሕ መምሪያ ለመስቀል በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፏል። ‎
Next article“መስቀል ኢትዮጵያን ለዓለም የገለጠ ሃይማኖታዊ እሴት ነው” ከንቲባ አዳነች አቤቤ