
ንግሥት ዕሌኒ ለመስቀል በዓል መከበር ማዕከላዊ ስዕል ናት። የክርስቶስን መስቀል ለመፈለግ ያደረገችው ጉዞ፤ የተጠቀመችበት የዕጣን ጢስ ጥበብ እና ያሳየችው አስደናቂ ጽናት በዓሉን ከደመራ ማቃጠል እና ከዕልልታ ሥነ ሥርዓት ባለፈ የእምነት፣ የተስፋ እና የቁርጠኝነት ተምሳሌት ያደርገዋል።
ታሪካዊ ዳራው እንደሚያስረዳው ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበት ቅዱስ መስቀል አይሁድ በቆሻሻ መጣያነት በከመሩት ቦታ ላይ ለብዙ ዓመታት ቆይቷል። መስቀሉን ለማውጣት እና ክብሩን ለመመለስ የተነሳችው ንግሥት ዕሌኒ በዕድሜ መግፋት የሚመጣ አካላዊ ድካም፣ የቦታው ርቀት፣ የቆሻሻ ክምሩ ግዝፈት ከዓላማዋ ሊያስቆማት አልቻለም።
ንግሥቲቱ ከሮም ቁስጥንጥንያ ተነሥታ ኢየሩሳሌም ከገባች በኋላ የገጠማት ፈተና ቀላል አልነበረም። መስቀሉ የተቀበረበትን ትክክለኛ ቦታ የሚያውቁ ሰዎች መረጃ ለመስጠት ፈቃደኛ ባለመኾናቸው ያጋጠማትን ተግዳሮት የተወጣችው ኪርያኮስ የተባለውን አረጋዊ በማግኘት እንደነበር ከማኅበረ ቅዱሳን ድረ ገጽ ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል።
ዕሌኒ ደመራ አስደምራ እጣን በማጤስ፣ የዕጣኑ ጭስ ወደ ላይ ወጥቶ ተመልሶ በማረፍ መስቀሉ ያለበትን ቦታ እስኪያመለክታት ያሳየችው ትዕግሥት እምነትን ከተግባራዊ ጥበብ ጋር ያጣመረችበት መንፈሳዊ ጽናት ተደርጎ ተወስዷል።
መስቀሉ ያለበት ቦታ ከተለየ በኋላ ከመስከረም 17 እስከ መጋቢት 10 ቀን በነበሩት ሰባት ወራት የቆሻሻ ክምሩን በማስቆፈር ያሳየችው ትጋት “ጽናት” የሚለውን ቃል በተግባር ይተረጉማል። የዚህ ሁሉ ጥረት የጽናት ፍሬ የኾነው የዕፀ መስቀሉ መገኘት የእርሷ የግል ስኬት ብቻ አይደለም። እውነት የቱንም ያህል በዘመናት ቆሻሻ ቢዳፈን በማይናወጥ ጽናት አንድ ቀን መውጣቱ እንደማይቀር ያረጋገጠ እና የመላው ክርስትናን ታሪክ የቀየረ ታላቅ ድል ነው።
የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ይህንን ታሪካዊ ተአምር መነሻ በማድረግ በየዓመቱ የደመራ እና የመስቀል በዓልን በታላቅ መንፈሳዊ ሥነ ሥርዓት ታከብራለች። በዓሉ ሲከበር እና ደመራ ሲበራ ታሪካዊነቱን ከማሰብ ባሻገር በሕይወታችን የተዳፈኑ እውነቶችን፣ የተቀበሩ ተስፋዎችን እና የራቁ ሕልሞችን በንግሥቲቱ አይነት ብርቱ ጽናት መፈለግን እንደሚያስተምር የእምነቱ አባቶች ይናገራሉ።
የመስቀል በዓል እውነት እና ብርሃን ከጨለማ እና ከመቃብር በላይ ሁሌም አሸናፊ መኾናቸውን የሚዘከርበት የጽናት በዓል ነው።
#አሚኮ #መስቀል #ኢትዮጵያ🇪🇹
#ባሕር_ዳር #መስከረም_16_2019_ዓ_ም
✍️ በስማቸው አጥናፍ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
