‎የግማደ መስቀሉ ወደ ኢትዮጵያ አመጣጥ እና የግሸን ደብረ ከርቤ ታሪክ

5

‎
‎የኢየሱስ ክርስቶስ ግማደ መስቀሉ ወደ ኢትዮጵያ መምጣት ከቀዳማዊ አጼ ዳዊት (1374 – 1404 ዓ.ም) የንግሥና ታሪክ ጋር ተያይዞ እንደኾነ ይነሳል።
‎
‎በ14ኛው ምዕተ ዓመት በአጼ ዳዊት ዘመነ መንግሥት በግብጽ የሚኖሩ የኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች እና ፓትርያርኩ በኦቶማን ቱርኮች ከፍተኛ እንግልት እና ስደት ይደርስባቸው ነበር።
‎
‎በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የምዕራብ ጎንደር ሀገረ ስብከት የስብከተ ወንጌል የሊቃውንት ጉባኤ ሠብሣቢ ሊቀ ማዕምራን ዳዊት አለነ እንደሚሉት በወቅቱ የግብጽ ፓትሪያርክ የነበሩት አቡነ ማቲዎስም በግብጽ የሚኖሩ ክርስቲያኖችን ወደ ኢትዮጵያ ወስደው ከመከራ እና ስቃይ እንዲታደጓቸው ለኢትዮጵያው ንጉሥ አጼ ዳዊት ደብዳቤ እንደጻፉላቸው ይናገራሉ።
‎
‎ንጉሥ አጼ ዳዊትም ደብዳቤው እንደደረሳቸው የግብጽ ክርስቲያኖችን ከደረሰባቸው ስቃይ እና መከራ ነፃ ለማውጣት ወሰኑ። የሰው ሕይወት ከመጥፋት ለመታደግ የግብጽ ሕይወት የኾነውን የዓባይን ወንዝ መገደብ እንዳለባቸው ወታደራዊ ትዕዛዝ አወጁ፤ ጦራቸውንም ይዘው በሱዳን በኩል ወደ ግብጽ ተጓዙ።
‎
‎ይህም በኢትዮጵያ ታሪክ ለዓባይ ግድብ መሠረት ከጣሉ ነገሥታት አንዱ እንደኾኑ በታሪክ ድርሳናት መስፈሩን ነው ሊቀ ማዕምራን ዳዊት አለነ የሚናገሩት።
‎
‎የዓባይን ወንዝ መገደብ ያዩት የግብጽ ገዥዎችም በፍርሀት እና በድንጋጤ ተዋጡ። ግድቡ እንዳይገደብና ክርስቲያኖቹ በሰላም እንዲኖሩና ነፃ እንዲኾኑ እንደሚያደርጉ ገልጸው ለአጼ ዳዊት የተማጽኖ ደብዳቤ ላኩ። ንጉሡም ይቅርታ አደረጉላቸው፤ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በጭንቅ እና በመከራ ውስጥ የነበሩት ክርስቲያኖች በሰላም መኖር ጀመሩ።
‎
‎እነዚያ ክርስቲያኖች ንጉሥ አጼ ዳዊት ላደረጉላቸው ታላቅ ውለታ “ምን እናድርግልዎ?” ብለው ጠየቋቸው። ንጉሥ አጼ ዳዊትም “ለእኔ ተራ የኾነ ሥጋዊ ሀብት አልፈልግም፤ የምፈልገው ወርቅና ብር ሳይኾን በእናንተ ዘንድ የሚገኘውን የክርስትና መሠረት የኾነውን የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ግማደ መስቀል(ቀኝ ክንፉን) እና ኩራተ ርስቱን ስጡኝ፤ ኢትዮጵያ ከመንበረ እስክንድርያ አንዷ አካል በመኾኗ የምትካፈለው በረከት ይህ ነው” በማለት ምላሽ መስጠታቸውን ሊቀ ማዕምራን ዳዊት አለነ ያብራራሉ።
‎
‎በኋላም በግብጽ እና በእየሩሳሌም ይኖሩ የነበሩ የሃይማኖት አባቶች በጋራ ተስማምተው ለንጉሥ አጼ ዳዊት ጥብቅ የምሥጋና ደብዳቤ፣ የጌታችን ግማደ መስቀል፣ የሾክ አክሊል የተደፋበት አልባሳት፣ የጌታችን ሥዕል፣ ከርቤ እና ሌሎች ንዋየ ቅዱሳትን ላኩላቸው።
‎
‎አጼ ዳዊት ከግብጻውያን በክብር የተቀበሉትን የጌታችን ግማደ መስቀል ይዘው ወደ ኢትዮጵያ ሲመለሱ፣ በመካከለኛው ኢትዮጵያ አካባቢ «ስናር» በተባለችው የድንበር ቦታ ላይ ከፈረስ ወድቀው ማረፋቸውን ጥንታዊ ድርሳናት ይመሰክራሉ። መስቀሉም በጊዜያዊነት «ውዛ» በተባለ ቦታ በአደራ ተቀምጦ ቆየ።
‎
‎በኋላም በኢትዮጵያ የክርስትና ታሪክ በጣም መንፈሳዊ እንደኾኑ የሚነገርላቸው የአጼ ዳዊት ልጅ አጼ ዘርዓ ያዕቆብ መስቀሉን ተረከቡት። እግዚአብሔርም ለአጼ ዘርዓ ያዕቆብ በራዕይ «አንብር መስቀልየ በዲበ መስቀል» (“መስቀሌን በመስቀለኛ ቦታ እንድታስቀምጥ ለአንተ ተሰጥቶሃል፤ የአባትህን አደራም ተወጣ”) ብሎ እንደገለጸላቸው ይነገራል።
‎
‎ባለራዕዩ ንጉሥ አጼ ዘርዓ ያዕቆብም ከብዙ ቦታ ፍለጋ በኋላ ግማደ መስቀሉን በደቡብ ወሎ በሚገኘው በታላቁ አምባሰል ተራራ ግሸን ደብረ ከርቤ ላይ እንዲያርፍ አደረጉ። የጌታችን የቀኝ እጅ ያረፈበት ግማደ መስቀል በ1440ዎቹ አካባቢ በታላቅ ክብር እንዳረፈ የቤተክርስቲያን ሊቃውንት በማስታወሻቸው አስፍረዋል።
‎
‎ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ግማደ መስቀሉ ግሸን ደብረ ከርቤ ያረፈበትን ቀን በማሰብ መስከረም 21 ቀን በየዓመቱ በድምቀት እንዲከበር ሥርዓት ተደነገገ። ኢትዮጵያውያንም መስከረም 21 ቀን ወደ ግሸን ደብረ ከርቤ በመሄድ በዓሉን በየዓመቱ በድምቀት እያከበሩት ይገኛሉ።
‎
‎#አሚኮ #መስቀል #ኢትዮጵያ🇪🇹
‎
‎#ባሕር_ዳር #መስከረም_16_2019_ዓ_ም
‎
‎✍️ ዘጋቢ፦ ቴዎድሮስ ደሴ
‎
‎የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous article“የተሰቀለውን ያመልካሉ፤ የተሰቀለበትንም ያከብራሉ”