
በቆሻሻ ክምችት ስር ለዘመናት የተደበቀው ያ ድንቅ ምስጢር በአንድ ታታሪ ንግሥት እልህ አስጨራሽ ፍለጋ እና በዕጣን ጢስ መሪነት ዳግም ብቅ ሲል ዓለምን ያስደንቃል ብሎ ማን አስቦ ነበር?
የመስቀል በዓል ተራ ባሕላዊ አከባበር ሳይኾን የክፋት ሴራ ተሸንፎ እውነት የነገሠበት፤ የተቀበረው ታሪክ ዘመኑን ጠብቆ ለብርሃን የበቃበትን ታላቅ የድል እና የተአምር ጉዞ የሚያዘክር ሕያው ታሪክ ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበት ቅዱስ መስቀል ለዘመናት እንዳይወጣ ተደርጎ ቢቀበርም በንግሥት እሌኒ ጽናት እና በደመራው ጢስ መሪነት ከተቀበረበት ወጥቶ ለዓለም ብርሃንን አጎናጽፏል።
ዛሬም ድረስ በየዓመቱ በመስከረም ወር አደባባዩን በብርሃን የሚሞላው እና እስከ ሰማይ የሚንቀለቀለው የደመራ እሳት ከተራ የዕንጨት ክምችት በስተጀርባ ያንን ጥንታዊ ታሪክ እና ምስጢር ይዞ የሚነሳ ልብ አንጠልጣይ መንፈሳዊ ትዕይንት ነው።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የሰሜን ጎጃም ሀገረ ስብከት የስብከተ ወንጌል ኀላፊ መልዓከምህረት ግሩም አለነ የሃይማኖቱ ተከታዮች የተሰቀለውን ክርስቶስን ያመልካሉ፤ የተሰቀለበትን ቅዱስ መስቀልም በታላቅ ክብር ያከብራሉ ብለዋል። የመስቀል በዓል የታሪክ መጀመሪያው የቀራኒዮ ኮረብታን መሠረት ያደረገ ሲኾን ከቀራኒዮ በፊት የነበረው ዘመን በትንቢት፣ በምኞት እና በተስፋ የተሞላ ነበር፤ ከቀራኒዮ በኋላ ግን መስቀል በተግባር የታየ፣ የተዳሰሰ እና ዛሬም ድረስ ሕያው ኾኖ ያለ እውነት ነው ባይ ናቸው።
ይህ በደመ ክርስቶስ የከበረ መስቀል ፈዋሽ፣ ኀያል እና ኀይል ሰጭ መኾኑንም አስረድተዋል።
ከእውነት ያፈነገጡ እና የክርስቶስን መስቀል የመቃወም ዓላማ የነበራቸው አካላት ለዘመናት ቅዱስ መስቀሉን በአፈር እና በቆሻሻ ክምችት ስር አዳፍነው ቢቀብሩትም እውነተኛው መስቀል ግን የራሱን ዘመን ጠብቆ ከመውጣት አልተከለከለም ነው ያሉት። የእውነት አምላክ ንግሥት እሌኒን ምክንያት አድርጎ መስቀሉ እንዲወጣ አድርጎታል ብለዋል። ዛሬ በደመቀ ሁኔታ የምናበራው ደመራም ንግሥት እሌኒ መሥቀሉ ያለበትን ስፍራ ለመፈለግ እንጨት እና ዕጣን አያይዛ የጸለየችበትን እና ጢሱ የመራባትን ታሪካዊ ምስጢር መነሻ ያደረገ ሥርዓት እንደኾነ ነው የገለጹት።
በአሁኑ ዘመን በመሪነት ያሉ ወንዶች የቆስጠንጢኖስን፣ በኀላፊነት ላይ ያሉ ሴቶች ደግሞ የንግሥት እሌኒን ታታሪነት እና በጎ ግብር ሊላበሱ እንደሚገባ መልዓከምህረት ግሩም አለነ መክረዋል።
ሰዎች ለትውልድ የሚጠቅሙ እና የታሪክ ማኅደር ለኾኑ ሀገራዊ እና ሃይማኖታዊ ቅርሶች ታላቅ ዋጋ መስጠትን ከመስቀሉ ታሪክ ሊማሩ ይገባል ብለዋል።
በዕለቱ ከደመራው የወጣው ጢስ ለቅዱስ መስቀሉ ሲሰግድ እንደታየው ሁሉ እኛም ሰብዓዊነታችን እንደ ዕጣን ውብ መዓዛ ያለው እና በሩቅ የሚጠራ መልካም ሥራ መገለጫችን ሊኾን ይገባል ነው ያሉት። ንግሥት እሌኒ መስቀሉን ስታገኝ “ይኸውና አለች” በማለት ያወጀችውን እና ቅዱስ ያሬድም “ዝንቱ ውዕቱ” በማለት የዘመረለትን እንዲሁም አዳም ወደ ገነት ሲመለስ መሰላል ኾኖ ያገለገለውን መስቀል ዛሬም ትውልዱ “እዮሃ” እያለ ታሪኩን በታላቅ ክብር እያስቀጠለው ይገኛል ነው ያሉት።
ሰዎች ከንግሥት እሌኒ ጀግንነትን፣ ታታሪነትን፣ ትሕትናን እና ባለራዕይነትን ሊማሩ ይገባልም ብለዋል። በዓሉም ሲከበር ሃይማኖቱ በሚያዘው እና ባሕሉን በማይበርዝ መልኩ ሊኾን ይገባል ነው ያሉት።
ደመራ የተሠበሠበ እንጨት እንደመኾኑ መጠን መልዕክቱ መሠብሠብን እና አንድ መኾንን ነው ብለዋል። ሰዎች በቅዱስ ዳዊት መዝሙር እንደተነገረው በኅብረት እና በአንድነት መኖርን የዘወትር ባሕላቸው ሊያደርጉት እንደሚገባም አንስተዋል።
#አሚኮ #መስቀል #ኢትዮጵያ🇪🇹
#ባሕር_ዳር #መስከረም_16_2019_ዓ_ም
✍️ በሰለሞን አንዳርጌ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
