
የመስቀል በዓል በየዓመቱ ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ሰው ልጆች ኃጢያት መከራ የተቀበለበትን፤ ደሙን ያፈሠሠበትን፤ ለዘመናት በአይሁዶች ተቀብሮ የነበረውን መስቀል ለመፈለግ የተደረገ ጥረትን፤ የብርሃን መገለጥን በማሰብ ይከበራል።
ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የማኅበራዊ ገጽ የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው የደመራ በዓል ንግሥት ዕሌኒ የተቀበረውን እና የተሠወረውን የክርስቶስን መስቀል ለመፈለግ በደመራ ጢስ መሪነት ተከትላ ቦታውን እንዳገኘች የሚገለጽበት እና እውነት እና ብርሃንን ፍለጋ የተደረገ ታላቅ ጽናት የሚታሰብበትም ነው።
✝️የመስቀል በዓል በኢትዮጵያ ታሪክ፣ ባሕል እና ማኅበራዊ ሕይወት ውስጥ ታላቅ ሥፍራ አለው። በዓሉን ወጣት ከአዛውንቱ፤ ሕጻናት ከትላልቆች ጋር እኩል የሚያከብሩት፤ ሃይማኖታዊ ሥርዓቶች በአደባባይ ጎልተው የሚታዩበት፤ እውነትን በጽናት መፈለግ እንደሚገባ የሚሰበክበት ነው።
በበዓሉ ወቅት ካህናት ልብሰተ ክህኖታቸውን ተጎናጽፈው የያሬድን ጥዑመ ዜማ እያሰሙ፤ መዘምራን በመዝሙር ልብሳቸው ደምቀው ዝማሬን እያሰሙ፤ አዛውንቶች በሀገራዊ የባሕል ልብስ ደምቀው፤ አባቶች ችቦን በእጆቻቸው ይዘው በደመራው አካባቢ በመገኘት ሁሉም በአንድነት ያከብሩታል።
የሀገር ውስጥ እና የውጭ ሀገራትን ጎብኝዎች ቀልብ የሚስብ ልዩ ሃይማኖታዊ ትርኢትም ይቀርብበታል። “እሰይ እልል በሉ ተገኘ መስቀሉ” እየተባለም በኅብረት ፈጣሪ ይመሰገንበታል፤ ስለ አንድነት፤ አብሮነት እና ስለ ሀገር ሰላም ይጸለይበታል።
✝️የመስቀል በዓል ከሃይማኖታዊ ሥርዓቱ ባሻገር ባሕል እና ማኅበራዊ ሕይወት ይበልጥ ይጎላበታል። ማኅበረሰቡ በየአካባቢው በአንድነት ደመራ በመሥራት እና በመለኮስ፤ የእርድ ሥርዓትን በማድረግ፤ አብሮ በመመገብ፤ የተጣላን በማስታረቅ፤ ለቀጣዩ ዓመት በሰላም ያድርሰን ብሎ በመሳል እና በተለያዩ ባሕላዊ ሥርዓቶች በአንድነት ያከብራሉ።
በኢትዮጵያ የሚከበሩ ሃይማኖታዊ እና ባሕላዊ የአደባባይ ክብረ በዓላት የኢትዮያን የቱሪዝም ኢኮኖሚኖ እያሳደጉ ይገኛሉ። ከእነዚህ በዓላት መካከል ደግሞ የመስቀል ሃይማኖታዊ በዓል አንዱ ነው።
ካህናት በልብሰ ተክህኖ ደምቀው፤ በጽናጽል፤ በከበሮ ውብ ዜማን እያዜሙ፤ መዘምራን በኅብረት ዝማሬን እያሰሙ፤ በምዕመናን እልልታ የሚደምቀው እና የተለያዩ ማራኪ ሃይማኖታዊ ሥርዓቶች የሚታዩበት የመስቀል በዓል በዩኔስኮ በማይዳሰስ ቅርስነት እንዲመዘገብ አድርጎታል።
ይህንን ድንቅ ሃይማኖታዊ በዓልን ለመታደም ከተለያዩ የዓለም ሀገራት በርካታ ጎብኝዎች ወደ ኢትዮጵያ ይመጣሉ፤ በካሜራ ሌንሳቸው ሃይማኖታዊ ሥርዓቱን ቀርጸው ለዓለም ያሳያሉ፤ በልባቸው የኢትዮጵያን ድንቅ እሴት ከትበው ይይዛሉ፤ የመስቀልን በዓል አክብረው ሌሎች ታሪካዊ ቦታዎችን፤ የቱሪዝም መዳረሻዎችን በመጎብኘት ቆይታቸውን ያራዝማሉ።
ደመራው ሲለኮስ 🔥 የሚታየው ድንቅ ሃይማኖታዊ እሴት እና አብሮነት ደግሞ ይበልጥ የጎብኝዎችን ቀልብ ይስባል።
✝️የመስቀል በዓል ከሃይማኖታዊ ሥርዓቱ ባሻገር የቱሪዝም መዳረሻ በመኾን የኢትዮጵያን የቱሪዝም ገቢ ያሳድጋል።
በየዓመቱ የሚከበሩ ሃይማኖታዊ እና ባሕላዊ ክዋኔዎችን፤ ብሔራዊ ፓርኮችን፤ ታሪካዊ ቦታዎችን እና ሌሎች መዳረሻዎችን ለመጎብኘት በርካታ የውጭ ሀገር ጎብኝዎች ወደ ኢትዮጵያ ይመጣሉ።
የሰላም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ እንደሚሉት በኢትዮጵያ በ2018 በጀት ዓመት በቱሪዝሙ ከ5 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ተገኝቷል። 1 ነጥብ 6 ሚሊዮን የውጭ ጎብኝዎች ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸውንም ገልጸዋል።
ከቀደመው ዓመት ጋር ሲነጻጸር ከ300 ሺህ በላይ የጎብኝዎች ጭማሪ አሳይቷል። ይህም የ21 በመቶ ዕድገት ማሳየቱንም ነው ያነሱት። በዚህ ዓመትም የደመራ በዓልን ጨምሮ የቱሪስት መዳረሻዎችን ማስፋት እና የገቢ ምንጭ ማድረግ ይገባል። ለዚህም እየተሠራ ነው።
#አሚኮ #መስቀል_በዓል #ቱሪዝም #ኢትዮጵያ🇪🇹
#ባሕር_ዳር #መስከረም_16_2019_ዓ_ም
✍️ ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
