
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በድምቀት ከሚከበሩ ሃይማኖታዊ በዓላት መካከል የመስቀል ደመራ በዓል አንዱ ነው። በክብረ በዓሉ ከሚከናወነው የሃይማኖታዊ ሥርዓት ባለፈ እሴቱን የጠበቀ አስደናቂ ባሕላዊ ክዋኔ የሚንጸባረቅበት በመኾኑ በዩኒስኮ የዓለም ቅርስነት ተመዝግቧል።
✝️ደመራ ምንድን ነው?
ከመስቀል በዓል አንድ ቀን ቀደም ብሎ የሚከናወነው የደመራ በዓል ይባላል። መስቀል በማውጣት፣ በአደባባይ በመሠባሠብ፣ ችቦ ወይም እንጨት በመደመር የሚለኮስበት እና ሃይማኖታዊ ክዋኔዎች የሚከወኑበት ሁነት ነው።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በባሕር ዳር አህጉረ ስብከት በገዳመ ዮርዳኖስ መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ቤተ ክርስቲያን መምህር እና የስብከተ ወንጌል ኀላፊ ለቤዛ ጥላሁን የደመራ በዓል የመስቀሉ ጥልቅ ፍቅር የሚገለጽበት በዓል ነው ብለዋል።
መምህሩ እንደሚያስረዱት ደመራ ማለት “ደመረ” ከሚለው የግዕዝ ግሥ የወጣ ሲኾን ጨመረ፣ አንድ አደረገ፣ አዋሐደ የሚል ትርጉም አለው። ደመራ የሚደመርበት ምክንያትም የኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል ለ300 ዓመታት ተቀብሮ ከቆየበት ስፍራ ለማውጣታ የተደረገውን የፍለጋ ሂደት እና መስቀሉ የተገኘበትን ምስጢር የሚያስረዳ ነው ብለዋል።
✝️መስቀሉ ከተደበቀበት እንዴት ተገኘ?
እደ መምህሩ ማብራሪያ የመስቀሉ ፍቅር ያደረባት ንግሥት ዕሌኒ የመስቀሉን ነገር ዘወትር እያሰበች፤ ብርሃነ መስቀሉም በልቧ ይመላለስባት ነበር፡፡ መስቀሉ የተደበቀበትን ቦታ ለማወቅ ጥራለች፣ በርካታ የአካባቢውን ሰው ጠይቃለች፣ አፈላልጋለች፣ ደክማለች፣ ግን በቀላሉ ለማግኘት አልቻለችም ነበር።
በኋላም ጸሎት እያደረገች፣ ፈጣሪዋን እየለመነች፣ ፍለጋዋን ቀጠለች። ጸሎቷ ሰምሮ “ኪራኮስ” በተባለው አይሁዳዊ ሽማግሌ አማካኝነት መስቀሉ የተደበቀበትን ስፍራ አቅጣጫውን አመላከታት። ብዙ እንጨት ደምራ፣ ነጭ እጣን ጨምራ እንድታቃጥለውም ነገራት። ጭሱ ወደ ላይ ከወጣ በኋላ እንደገና ወደ መሬት ሲመለስ የሚያመላክተው መስቀሉ የተቀበረበት ቦታ እንደኾነም ጠቆማት።
ንግሥት ዕሌኒም የተባለችውን ፈጸመች። ደመራ አስደመረች። ደመራውም በጸሎት ተባርኮ ተለኮሰ። የደመራው ጭሱ ወደ ላይ ወጥቶ እንደገና ወደ መሬት ተመለሰ። ይህም መስቀሉ የተደበቀበት ቦታ መኾኑ ታወቀ። በዚህ የጭስ ጠቋሚነት ቁፋሮ ተጀመረ። ከስድስት ወራት ቁፋሮ በኋላ መጋቢት 10 መስቀሉ ተገኘ፤ ተደብቆ ከኖረበት ወጣ።
✝️ መስቀሉን ፈልጎ ለማግኘት የተደረገውን ሂደት እና የተደበቀበት ቦታው የተመላከተበትን ዕለት ለማሰብ የደመራ በዓል እየተከበረ መቀጠሉን አስረድተዋል።
✝️ መስቀሉ ከተቀበረበት ተቆፍሮ የወጣው መጋቢት 10 በመኾኑ ይህም በዐቢይ ጾም ወቅት ስለኾነ ይህንን ዕለት በመስከረም 17 ታስቦ እንዲውል ስለተደረገ ነው ብለዋል።
✝️ በተጨማሪም ለመስቀሉ ማረፊያ የተሠራው ቤተ መቅደስ የከበረበት ወይም የተቀደሰበት በመስከረም 17 በመኾኑ በዕለቱ የመስቀል በዓል ተከብሮ እንዲውል ስለመደረጉም አብራርተዋል።
✝️ ደመራው ለመስቀሉ መገኘት፣ መስቀሉም ለደመራው መከናወን ምክንያት መኾናቸውንም አስረድተዋል።
#አሚኮ #Meskel #Demera #Ethiopia🇪🇹
#ባሕር_ዳር #መስከረም_16_2019_ዓ_ም
✍️ በአሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
