🕊️ የግጭት ምንጭ ይድረቅ፣ የሞት እርምም ይውጣ✨

11

 

በአማራ ክልል ባለፉት ሦሥት ዓመታት በዘለቀው የሰላም እጦት ምክንያት ከፍተኛ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ውድመት ደርሷል። ማኅበረሰቡ በደስታና በሀዘን እንዳይገናኝ፣ ማኅበራዊ ግንኙነት እንዲገታ አድርጎ ቆይቷል። በርካቶችን ለሥነ-ልቦና ጉዳትም ዳርጓል።

​ወንድም ወንድሙን እያደማ ቆይቷል። ግጭቱን ለማስቆም በርካታ የሰላም ጥሪዎች ቀርበዋል። የሰላም በሮችም ተከፍተዋል። ይህንን አስከፊ በደል እና ግፍ በመገንዘብ የሰላም አማራጭን የተቀበሉ የቀድሞ ታጣቂዎች በርካታ ናቸው።

እነዚህ ታጣቂዎች የተበደለውን ሕዝብ ለመካስም የሰላም አማራጭ መቀበላቸውን በተለያዩ አካባቢዎች አሳይተዋል፤ አሁንም የሰላም አማራጭን እየተቀበሉ እየገቡ ነው። ቀደም ብለው የገቡትም ከማኅበረሰቡ ጋር እየተቀላቀሉ የተረጋጋ ሕይወት እየመሩ ይገኛሉ።

በክልሉ የሰላም አማራጭ ተቀብለው የተረጋጋ ሕይወት እየመሩ ከሚገኙት የቀድሞ ታጣቂዎች መካከል በኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር የሚገኙት ባለታሪካችን አንዱ ናቸው።

​ባለታሪካችን እንደተናገሩት በተሳሳተ መንገድ ወደ ጫካ በመውጣታቸው ሕዝቡን ሲበድሉ መቆየታቸውን በጸጸት ይገልጻሉ።

አሁን ላይ ግን የነበራቸውን የተሳሳተ አስተሳሰብ በመተው በመንግሥት የሰላም አስከባሪ አባል በመኾን እያገለገሉ ይገኛሉ።

የሰላም አማራጭን በመቀበላቸው “ማኅበረሰቡም እረፍት አግኝቷል፤ እኛም ሰላም አግኝተናል” ይላሉ። አርዓያ በመኾን ሌሎችም የሰላም አማራጭ እንዲቀበሉ ማድረጋቸውን ጠቁመዋል።

አሁን ላይ የተረጋጋ ሕይወት እየመሩ እንደሚገኙም ገልጸዋል። ሌሎችም በጫካ ኾነው የማኅበረሰቡን ሕይወት ከመረበሽ ይልቅ የሰላም አማራጭን መቀበል የሕሊና እርካታ እንደሚሰጥ ነው ያስገነዘቡት።

የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ሰላም እና ጸጥታ መምሪያ ኀላፊ አወል እንድሪስ በብሔረሰብ አሥተዳደሩ
ከኅብረተሰቡ እና ከጸጥታ አካላት ጋር በቅንጅት በተሠራው ሥራ ሰላሙ እየተረጋጋ መምጣቱን ገልጸዋል።

በተለይም የሀገር ሽማግሌዎችን፣ ወጣቶችን እና እናቶችን በማደራጀት ሕዝቡን የሰላሙ ባለቤት ማድረግ መቻሉን አንስተዋል።

ከአጎራባች ዞኖች ጋር በመተባበር ቀጣናውን ሰላማዊ የማድረግ ሥራ እየተሠራ ነውም ብለዋል።

በዚህም በርካታ የቀድሞ ታጣቂዎች የሰላም አማራጭን በመከተል የተሃድሶ ሥልጠና ወስደው በሰላም ማስከበር እና በተለያዩ የሥራ ዘርፎች ተሰማርተው የኢኮኖሚ ተጠቃሚ እየኾኑ ይገኛሉ ነው ያሉት።

አሁንም የሰላም በሩ ክፍት መኾኑን የገለጹት ኀላፊው በአፈሙዝ የሚመለስ ጥያቄ የለም፤ ኑ በጋራ ሀገር እናጽና እና ልማት እናፋጥን የሚል ጥሪ አስተላልፈዋል።

#አማራክልል #ሰላም #ኢትዮጵያ 🇪🇹 #አሚኮ

#ባሕር_ዳር #መስከረም_15_2019_ዓ_ም

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleየሰማዩ ንስር፣ የሉዓላዊነት ጠበቃ!
Next articleየይለፍ ቃልዎ ጠንካራ ነው ወይስ? ምንስ ሊገጥመዎት ይችላል?