
119ኛው የመከላከያ ሠራዊት ቀን ተከብሯል።
በመከላከያ ሠራዊት ቀን መልዕክት ያስተላለፉት የጦር ኀይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የቀጣናው አስተማማኝ ኀይል መኾኑን ገልጸዋል። ሊያፈርሱት የከጀሉትን ያፈርሳል እንጂ በመከላከያ ሠራዊት መቃብር ላይ የሚመሠረት የሽግግር መንግሥት የለም ብለዋል።
የውስጥ ባንዳዎች የኢትዮጵያን ዕድገት በስጋት ከሚመለከቱ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር እየሠሩ መኾናቸውን ተናግረዋል።
ሕገ ወጡ ሕወሃት አራት እንቅፋት የመታው ፍጡር ነው ያሉት ፊልድ ማርሻሉ በዘመቻ ሕግ ማስከበር፣ በዘመቻ ኅብረ ብሔራዊ አንድት፣ ፕሪቶሪያን በወለደው ሦሥተኛው ዘመቻ እና ለአራተኛ ጊዜ ወደ ቆቦ፣ ላሊበላ፣ ተኩለሽ እና አካባቢው መጥቶ መመታቱን አንስተዋል። አሁን ወደ ባልደረባው ሻዕቢያ ሄዷል ነው ያሉት።
ሕገ ወጡ ሕወሃት ከጥፋት የማይመለስ ቡድን መኾኑን ያስረዱት ፊልድ ማርሻሉ ሕወሃት ከተቻለው አምስተኛ እንቅፋት እንዳይመታው ከማድረግ የሚመልሰው አዕምሮ የለውም፤ ነገር ግን አምስተኛ ዕድል እንዲኖረው አናደርግም ብለዋል።
የትግራይ እናቶች፣ ወጣቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች በሕወሃት የጦርነት አዙሪት ያላቸውን እና ሊኖራቸው የሚገባውን ሁሉ ማጣታቸውን ተናግረዋል። ልጆቻቸውን በጉልበት በማስገደድ በጦርነት በመማገድ ሁለት ትውልድ አሳጥቷቸዋል፤ የትውልድ ቅብብሎሹን አዛብቷል፤ የነበራቸውን ጥሪት አሳጥቷቸዋል፤ እርዳታ ጠባቂ አድርጓቸዋል ነው ያሉት። ነገር ግን ከጎናቸው ቆመን እየተከላከልንላቸው እንገኛለን ብለዋል።
ሕወሃት በሁለት ሳምንት ለመቅበር አቅዶ ሁለት ሳምንት ሳይሞላው ተቀብሯል ብለዋል። ትግራይ ክልል አዳዲስ ሃሳብ፣ አዲስ አመራር፣ ሰላም እና ልማት ብቻ ያስፈልጋታል ነው ያሉት።
የግማሽ ምዕተ ዓመት የማርክሲስት እና ሌኒኒስት መስመር የትግራይ ሕዝብ ፍዳውን በልቶበታል ያሉት ጠቅላይ ኤታማዦር ሹሙ ሁሉም ኢትዮጵያውያን ሊያግዛቸው እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
መከላከያ ሠራዊትን ሊያፈርሱ ቋምጠው ነበር፤ ይህ የታሪካዊ ጠላቶች እርኩስ ሀሳብ ተመትቷል፤ ሠራዊቱ በፍትሕ እየተመራ ሰባት የጽምዶ ቡድኖችን፣ ሦሥት የጀርባ የውጭ ኀይሎችን አሸንፏል ነው ያሉት።
#የመደመር_መንግሥት!
#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ!🇪🇹
#ባሕር_ዳር #ጥቅምት_15_2019_ዓ_ም
ዘጋቢ፦ አድኖ ማርቆስ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
