የኢትዮጵያ ሕልውና እና የግብጽ የዘመናት ስውር ሴራ!

2
🇪🇹
ግብጽ ባለፉት ዘመናት በኢትዮጵያ ላይ ስትሸርብ የኖረችው ውሥብሥብ፣ ስውር እና ዘርፈ ብዙ ጠላትነት የተመዘገበ የታሪክ እውነታ ነው።
የካይሮ ፖሊሲ አቀናባሪዎች ዘመን ባሳለፉ ቁጥር ዋና ግባቸው አንድ ብቻ ነው፤ ይህም ኢትዮጵያ እንዳታድግ፣ ጠንካራ ማዕከላዊ መንግሥት እንዳይኖራት፣ ተፈጥሮአዊ ሀብቷን እንዳትጠቀም በማድረግ በምሥራቅ አፍሪካ ያላትን የጅኦፖለቲካዊ እና የዲፕሎማሲ የበላይነት ማዳከም ነው።
👉የወታደራዊ፣ ጅኦፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ሴራዎች፦ ግብጽ የዓባይን ውኃ ሙሉ በሙሉ የመቆጣጠር ታሪካዊ ፍላጎቷን ለማስጠበቅ ስውር እና ውሥብሥብ አጥፊ ስልቶች ተጠቅማለች። የመጀመሪያው ግብጽ በቀጥታ ውጊያ ኢትዮጵያን ማሸነፍ እንደማትችል የታሪክ አጋጣሚዎች (እንደ ጉንደት እና ጉራዕ ውጊያዎች) ስላስተማሯት ስልቷን ወደ ውክልና ጦርነት ቀይራለች።
ሻዕቢያን፣ የሀገር ውስጥ አሸባሪዎችን፣ ከፋፋይ ቡድኖችን እና ሆደ-አደር ባንዳዎችን በገንዘብ፣ በስለላ እና በዓለማቀፍ ዲፕሎማሲያዊ ድጋፍ በማጠናከር ኢትዮጵያ በውስጥ ግጭት እንድትታመስ እየሠራች ነው።
ኢትዮጵያ የታላቁ ሕዳሴ ግድብን ጨምሮ በዓባይ ተፋሰስ ላይ ማናቸውንም የልማት ፕሮጀክቶች ስታቅድ ግብጽ ከዓለም ባንክ፣ ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት አይኤምኤፍ እና ከአረብ ፈንዶች ብድር እና እርዳታ እንዳታገኝ ጠንካራ የዲፕሎማሲ ጫና ስታደርግ ቆይታለች።
በቀይ ባሕር፣ በአፍሪካ ቀንድ እና በጎረቤት ሀገራት አቅራቢያ ወታደራዊ ሰፈሮችን በመሥራት ስትራቴጂካዊ ጥምረቶችን በመፍጠር ኢትዮጵያን በጅኦፖለቲካዊ መንገድ ለመክበብ ያላሰለሰ ጥረት ስታደርግ መቆየቷም ሌላኛው ድብቅ ሴራዋ ነው።
👉የዘርፉ ምሁራን እና የታሪክ ምስክሮች ምን ይላሉ? በ “ፉቱህ አል-ሀበሻ” መጽሐፉ ላይ እንደተመዘገበው የግብጽ እና የአካባቢው ኀይሎች በኢትዮጵያ ላይ የነበራቸው ፍላጎት እና ጣልቃ ገብነት የረጅም ዘመን ታሪክ ያለው መኾኑን ያሳያል።
የኢትዮጵያን የወደፊት ጥንካሬ እና ስትራቴጂካዊ የበላይነት ለመስበር ግብጽ ከጥንት ጀምሮ የውስጥ ባንዳዎችን እንደ መሳሪያ ስትጠቀምበት እንደነበር የታሪክ ሰነዶች ያረጋግጣሉ።
የታሪክ እና የፖለቲካ ሳይንስ ምሁራን ፕሮፌሰር ያዕቆብ አርሳኖ እንደሚሉት ግብጽ ከ1929 እና ከ1959 የመልካም ጉረቤትነት እና የፍትሐዊነት መርህን ከሚጥሱ የቅኝ ግዛት ውሎች ባሻገር፣ ኢትዮጵያን “ያለ ውኃ እና ያለ ልማት” ለማስቀረት የሄደችበት የዲፕሎማሲ ርቀት የፍትሐዊነትን መርህ የካደ ነው። ግብጽ ውኃውን እንደ ፖለቲካዊ የበላይነት ማስጠበቂያ እንጂ እንደ የጋራ ተፋሰስ ሃብት አይታው አታውቅም ይላሉ።
👉የኢትዮጵያ አይበገሬነት እና የተመዘገቡ ተጨባጭ ስኬቶች፦ ግብጽ እና ተላላኪዎቿ ያሴሩት ሴራ ሁሉ በኢትዮጵያውያን ጽናት እና አርበኝነት ፊት ፈራርሷል።
ለዚህ ማሳያ ኢትዮጵያ ያለ ምንም የውጭ ብድር እና እርዳታ በሕዝቧ አስተዋጽኦ የታላቁ ሕዳሴ ግድብን ገንብታ ማጠናቀቋ ነው። ይህም የግብጽ የቅኝ ግዛት ውሎችን ውድቅ በማድረግ “ፍትሐዊ የውኃ አጠቃቀምን” በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕጋዊ መሠረት አስይዟል።
የግብጽ ስውር ሴራ እና የባንዳዎች ሴራ የኢትዮጵያን የዕድገት ጉዞ ለጊዜው ሊያደናቅፉ ቢችሉም የሀገሪቱን ታሪካዊ አይበገሬነት ግን ሊሰብሩት አልቻሉም።
ኢትዮጵያ የዓባይን ውኃ በፍትሐዊነት የመጠቀም መብቷን በተግባር አረጋግጣለች፤ ወደፊትም በቀጣናው ያላትን የጎላ ሚና አጠናክራ ትቀጥላለች።
ዘጋቢ፦ ቴዎድሮስ ደሴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous article“መከላከያ ሠራዊት ሊያፈርሱት የከጀሉትን ያፈርሳል” ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ
Next article“ለጠላት መሳሪያ አንኾንም፤ ሰላምን ቀዳሚ ምርጫ አድርገናል” የቀድሞ ታጣቂዎች