
የሀገርን ሕልውና ለማስቀጠል የተደወለው የሰላም ደወል እና የቀረበው ጥሪ ከተስተጋባ ሰነባብቷል። አሁንም የሰላም በሩ አልተዘጋም፤ የሰላም ተስፋውም እየሰፋ ይገኛል።
ጥሪው ተጠናክሮ በቀጠለበት በዚህ የሰላም ደወል ለሀገር እና ለሕዝብ ቅድሚያ የሰጡ በርካታ ታጣቂዎች ምርጫቸውን አስተካክለው ወደ ሰላማዊ ሕይወት ተመልሰዋል። ይህ የሰላም ጥሪ ሕዝብን ከግጭት አውድ ወደ ልማት የሚያሸጋግር ጠንካራ ድልድይም ኾኗል።
እየተፈጠረ ያለው የሰላም ምኅዳር ለልማት እና ለዕድገት የሚያዘጋጅ ትልቅ ተስፋ ኾኖ ቀጥሏል።
የአማራ ክልል ባለፉት ዓመታት በርካታ ቀውሶች ደርሰውበታል፤ የሰላም እና የልማት ሥራዎችም ተስተጓጉለዋል። ይህን የተገነዘቡ በርካታ የቀድሞ ታጣቂዎች የተከፈተውን የሰላም በር በመጠቀም የተዘረጉ የሰላም እጆችን መጨበጣቸውን ቀጥለዋል። የተረጋጋ ሕይወትም እየመሩ ናቸው።
በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች የሰላም አማራጩን የተከተሉ የቀድሞ ታጣቂዎች በውዥንብር “የሕዝብ ጥያቄ እናስመልሳለን”በሚል ስህተት ወደ ጫካ ገብተው እንደነበር ያስታውሳሉ። በጫካ ቆይታቸው በኅብረተሰቡ ላይ የሚፈጸመው ዘረፋ እና ጭካኔ የተሞላበት ድርጊት ሕሊናቸው የማይቀበለው እና ትክክል ያልኾነ ተግባር እንደነበር ተናግረዋል። ሲሠሩ በቆዩት ሥራ ቤተሰብንም ኾነ ማኅበረሰብን ሲያስቸግሩ እንደቆዩም አንስተዋል።
የሰላም አማራጭ በመከተላቸው እነሱም፣ ቤተሰባቸውም ኾነ ሀገር የሰላም እፎይታ አግኝቷል ይላሉ። ወደ ሰላም ከተመለሱ በኋላም የተሀድሶ ሥልጠና መውሰዳቸውን ነው የገለጹት። የሰላም አማራጭ በመከተላቸው የተረጋጋ ሕይወት እየመሩ እንደሚገኙም ተናግረዋል። ወደ መደበኛ ሥራቸው ተመልሰው ኑሮአቸውን እየመሩ መኾናቸውንም ገልጸዋል። በግጭት የሚገኝ ትርፍ የለም ነው ያሉት።
የትግል ሂደቱ የተሳሳተ እና ዓላማ የሌለው በመኾኑ ሀገርን ለጠላት አሳልፎ የሚሰጥ፣ አላስፈላጊ መስዋዕትነት የሚያስከፍል፣ ቤተሰብን እና ራስን ለዳግም ጉዳት የሚያጋልጥ ነው ያሉት የቀድሞ ታጣቂዎቹ የሀገርን ሕልውና የሚጎዳ ነውም ብለዋል።
ከአላስፈላጊ መስዋዕትነት በመውጣት እና ጥያቄዎችን በውይይት መፍታት ብቸኛው አማራጭ መኾኑንም ተናግረዋል። አሁንም በጫካ የሚገኙ ታጣቂዎች የሰላም አማራጩን ተቀብለው ወደ ኅብረተሰቡ በመቀላቀል የተረጋጋ ሕይወት መምራት እንደሚገባቸውም ጥሪ አቅርበዋል።
የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ በክልሉ የመንግሥት ምሥረታ ወቅት ባደረጉት ንግግር ግጭት
ክልሉን ለዘርፈ ብዙ ቀውሶች የሚዳርግ እና የልማት ጎዳናን የሚያቀጭጭ መኾኑን ገልጸዋል።
ግጭት ለማንም አይበጅም ያሉት ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ በተለይም በጫካ የሚገኙ አካላት የሕዝቡን ሰላም እና ለልማት ቅድሚያ በመስጠት የተዘረጋውን የሰላም መንገድ እንዲከተሉ ጥሪ አቅርበዋል።
የክልሉን የሀገርን ሰላም በማጽናት የተጀመረውን የልማት ጎዳና ማስቀጠል እንደሚገባም ተመላክቷል።
#የመደመር_መንግሥት!
#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ!
#ባሕር_ዳር #ጥቅምት_16_2019_ዓ_ም
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
