
የአማራ ክልል ገጠር ልማት ዘርፍ የ2019 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ዕቅድ አፈጻጸምን እየገመገመ ነው።
በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የገጠር ልማት ዘርፍ አሥተባባሪ ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር) ከፍተኛ የልማት እንቅስቃሴ በማድረግ እና ድህነትን በመቀነስ፣ በክልሉ በሰው ሠራሽ እና በተፈጥሮ አደጋ የገጠሙ ችግሮችን ሊቀለብስ የሚችል የልማት ሥራ ማከናወን ያስፈልጋል ብለዋል።
ለዚህም ውጤታማ ሥራ ለማከናወን ታቅዶ ወደ ሥራ ተገብቷል ነው ያሉት። በመጀመሪያ ሩብ ዓመቱም ሁሉም ቢሮዎች ከላይ እስከ ታች ዕቅድ እና ሥራን የማናበብ፣ የታችኛው የመሪዎች እርከን ያለውን ኃይል የማብቃት እና በጠራ ዕቅድ ላይ ተመሥርቶ ተግባራትን መፈጸም እንዲችል በማድረግ በኩል ውጤታማ ሥራ መከናወኑን ተናግረዋል።
የዚህ ዓመት የቴክኖሎጅ ሽግግር ሥራውም ያለምንም ችግር በውጤታማነት መከናወኑንም ገልጸዋል። ባለፉት 90 ቀናት ሁሉም ቢሮዎች ከላይ እስከ ታች ዕቅድን የማናበብ፣ የታችኛውን መሪ የማብቃት እና የቴክኖሎጂ ሽግግር ሥራዎችን ያለምንም ችግር በውጤታማነት የማከናወን ተግባራት መከናወናቸውን አብራርተዋል።
እየተካሄደ የሚገኘው የዕቅድ ግምገማ ባለፉት 90 ቀናት በተቋማት የተሠሩ ሥራዎችን በመፈተሽ፣ በቀጣዩ ሩብ ዓመት ልዩ ትኩረት የሚሹ እና ከመጀመሪያው ሩብ ዓመት ያደሩ ተግባራትን አካትቶ ለመፈጸም ታስቦ የተዘጋጀ መኾኑን ገልጸዋል።
በመጀመሪያው ሩብ ዓመት የታዩ “ስኬቶችን እንደ መስፈንጠሪያ፤ ተግዳሮቶችን ደግሞ መማሪያ በማድረግ” የበጀት ዓመቱን ዕቅድ በልዩ ተነሳሽነት እና ውጤታማነት መፈጸም እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
