
“በአፍሪካ ወደ ሰላም የሚወስዱ መንገዶች፣ ኢኮኖሚያዊ ሉዓላዊነት እና ጂኦፖለቲካዊ ለውጥ” በሚል መሪ መልዕክት በባሕር ዳር ሲካሄድ የሰነበተው 12ኛው የጣና ከፍተኛ የአፍሪካ ጸጥታ ፎረም ተጠናቅቋል።
በማጠቃለያ መርሐ ግብሩ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት
የጋና ፕሬዝዳንት እና የጣና ፎረም ሠብሣቢ ጆን ድራማኒ ማሃማ ፎረሙ ስኬታማ እንደነበር ገልጸዋል። መስተንግዶውም አስደናቂ እንደኾነ ተናግረዋል።
በፎረሙ የተደረጉ ውይይቶቾ ግልጽ እና ጥልቅ እንደነበሩም ገልጸዋል። ፎረሙ ስኬታማ እንዲኾን ላደረጉ ሁሉ ምሥጋና አቅርበዋል።
በአፍሪካ የሰላም እና ደኅንነት ሁኔታ የቀረበውን ሪፖርት ወስደን እንደምንመረምረው እና አፍሪካን የሚያሰቃዩትን በርካታ ግጭቶች ለመፍታት ጠቃሚ እንደሚኾንም ተስፋ አደርጋለሁ ነው ያሉት።
መነጋገር ጥሩ ነገር ነው፣ በውይይት መፍትሔ ለመፈለግ መሞከርም ጥሩ ነገር ነው፤ ነገር ግን መተግበር የበለጠ የተሻለ ነው ብለዋል። ከውይይት ወደ ተግባር መሸጋገር አለብንም ነው ያሉት።
በፎረሙ የተገኘው ልምድ ሰላም ማለት የኢኮኖሚ ውህደት እና በአንድ ድምጽ መናገር መኾኑን ነው ብለዋል። ሰላም ማለት የወገኖቻችንን የጎንዮሽ መገፋፋት ማብቃት ነው። ወጣቶች፣ ሴቶች እና አካል ጉዳተኞች ሙሉ አቅማቸውን እንዲጠቀሙ ዕድል የሚሰጥ አሳታፊ ማኅበረሰብ መፍጠር ነው ብለዋል።
ዓለም አቀፋዊ በኾነ መንገድ ማሰብ አለብን፣ ነገር ግን በአካባቢ ደረጃ ተግባራዊ ሥራ መሥራት አለብን ነው ያሉት። የአፍሪካ መሪዎች ለሕዝቦቻቸው ተጠቃሚነት መሥራት እንደሚገባቸውም ተናግረዋል።
እንደመሪ የምንቆመው ለሕዝባችን ሊኾን ይገባል፤ ለዜጎቻችንም የሚጨበጥ ጥቅም መፍጠር አለብን ነው ያሉት።
ጣና ፎረም በአፍሪካ ላይ የተደቀኑብንን ፈታኝ ሁኔታዎች በግልጽ እንድንመረምር እና እንድንወያይ ዕድል ሰጥቶናል ብለዋል። እዚህ የተወያየንባቸውን ጉዳዮች ለመተግበር ቁርጠኛ ኾነን ከአሁኑ ሰዓት ጀምሮ መነሳት አለብን ነው ያሉት።
የጣና ፎረም ስኬታማ እንዲኾን ላደረጉት የኢትዮጵያ መንግሥት እና ሕዝብ እንዲሁም ደማቅ መስተንግዶ ላደረገችው ባሕርዳርም ምሥጋና አቅርበዋል።
#የመደመር_መንግሥት!#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ!🇪🇹
#ባሕር_ዳር #ጥቅምት_15_2019_ዓ_ም
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
