
የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ዓለምአንተ አግደው የፍትሕ ተደራሽነትን ማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ በኢትዮጵያ ከአየርላንድ አምባሳደር ጋር ተወያይተዋል።
ውይይቱ የፍትሕ ተደራሽነትን ማጠናከር፤ የፍርድ ቤቶችን አገልግሎት አሰጣጥ ምቹ እና ቀልጣፋ ማድረግ፤ ባሕላዊ ፍርድ ቤቶችን እና አማራጭ የሙግት መፍቻ ዘዴዎችን ማስፋት፤ እንዲሁም የተከላካይ ጠበቆችን ሚና ማጎልበት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ነበር።
በተጨማሪም በዘመናዊ የዳኝነት ቴክኖሎጂዎች በመታገዝ የፍትሕ ሥርዓቱን ተደራሽ የማድረግ አስፈላጊነት ላይ መክረዋል።
በቆይታቸውም የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ዓለምአንተ አግደው የዳኝነት እና የፍትሕ ሥርዓቱን ለማዘመን እና ተደራሽ ለማድረግ እስካሁን ስለተከናወኑ ሥራዎች ገለጻ ያደረጉ ሲኾን የተጀመሩ ማሻሻያዎችን አጠናክሮ ለማስቀጠል ከኤምባሲው ጋር በትብብር ለመሥራት ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸዋል።
የአየርላንድ አምባሳደር ሲራን ማደን በበኩላቸው ለተደረገላቸው አቀባበል እና ገለጻ አመሥግነው፣ በጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የተከናወኑ ሁሉአቀፍ የለውጥ እና የማሻሻያ ሥራዎችን ተዘዋውረው በመጎብኘት ባዩት ነገር መደሰታቸውን ገልጸዋል።
አምባሳደሩ አክለውም ኤምባሲያቸው የፍትሕ ሥርዓቱን ይበልጥ ተደራሽ እና ዘመናዊ ለማድረግ ከጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ጋር በትብብር እንደሚሠራ እና በቀጣይም በለውጥ ፕሮጀክቶች ላይ ተጨማሪ ውይይት እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።
#የመደመር_መንግሥት!#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ!🇪🇹
#ባሕር_ዳር #ጥቅምት_15_2019_ዓ_ም
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
