
የኢትዮጵያ አየር ኅይል የሀገርን ሉዓላዊነት እና ደኅንነት ለማረጋገጥ ሰማይን በንስር ዐይን እየቃኘ 90 ዓመታትን ተሻግሯል።
ይህ ታሪካዊ አየር ኃይል የኢትዮጵያን እና የቀጣናውን ሰላም ሲያስከብር የኖረ የጀግኖች ቤት ነው።
የኢትዮጵያን ዳር ድንበር ከማስከበር አልፎ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ተልዕኮዎችን በብቃት መወጣት ችሏል። በ1954 ዓ.ም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሥር ኾኖ በኮንጎ ዓለም አቀፍ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ላይ ተሳትፏል።
ታንዛኒያ ነፃ ከወጣች በኋላም ጎረቤቷ ሞዛምቢክ በፖርቹጋል ሥር በነበረችበት ጊዜ የኢትዮጵያ አየር ኅይል በራሱ አውሮፕላኖች እና አብራሪዎች የታንዛኒያን የአየር ክልል ለወራት ማስከበሩን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) መናገራቸው ይታወሳል።
አየር ኅይሉ የሀገር ደጀንነቱንም በተግባር አረጋግጧል። በዚያድ ባሬ ወረራ ጊዜ አስደናቂ ጀብዱ በመፈጸም የካራማራ ድልን አስገኝቷል። ኢትዮጵያንም አኩርቷል።
በ1990ዎቹ የባድመ ጦርነት ወቅት ለመከላከያ ሠራዊቱ ትልቅ መከታ በመኾን የጠላትን የሎጂስቲክስ መስመር በመበጠስ እና የአየር ክልልን በማስከበር ለምድር ጦሩ ስኬት መንገድ ጠርጓል።
የኢፌዴሪ አየር ኀይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ ከሀገር በመለስ በተለያዩ ሀገራት በመሰማራት ለዜጎች እፎይታን የሰጠው ተቋሙ በኢህአዴግ ዘመን ተዳክሞ እንደነበር ገልጸዋል።
ከ2010 ዓ.ም በመጣው ለውጥ እና በተደረገለት ሪፎርም ወደ አስደናቂ ደረጃ ተሻግሯል። አየር ኅይሉ አሁን ላይ የብሔራዊ ኩራት፣ የቴክኖሎጂ ዕድገት እና የተልዕኮ ጽናት ተምሳሌት በመኾን ቀጥሏል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) እንደገለጹት አየር ኅይሉ ኢትዮጵያን ለመድፈር ለሞከሩ ኀይሎች ኹሉ ሁነኛ መድኃኒት በመኾን የሀገር ህልውናን በማጽናት የማይጠፋ አሻራ አኑሯል።
የአብራሪዎች እና የቴክኒሻኖች ማሠልጠኛ ኮሌጆችን በማጠናከር ብቁ ባለሙያዎችን የማፍራት፣ አውሮፕላኖችን ከማደስ አልፎ መለዋወጫዎችን እስከማምረት የደረሰ የሪፎርም ሥራ መከናወኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቁመዋል። የምርምር እና ዲዛይን ሥራዎችን የማከናወን ተግባራት በመፈጸም ተቋሙን የማዘመን እና የመፈጸም አቅሙን የማሳደግ ሥራ በትኩረት ተሠርቷል።
ዘመናዊ የውጊያ አውሮፕላኖችን፣ የድሮን ቴክኖሎጂዎችን፣ የላቁ የክትትል ሥርዓቶችን እና ጠንካራ የሳይበር አቅምን ማስታጠቅም በትኩረት ተሠርቷል።
የወደፊቱ አየር ኅይል ከፍተኛ የቴክኖሎጂ ልህቀትን የሚጠይቅ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳረጋገጡት የሰውን ሕይወት ከመገበር ይልቅ በቴክኖሎጂ ታግዞ ጦርነትን በአጭሩ ለመቋጨት አሁን ያለውን የውጊያ አቅም በ2030 ወደ አምስተኛው ትውልድ ለማሸጋገር ራዕይ ተነድፎ እየተሠራ ነው።
#AMECO #Ethiopia #airforce
#ባሕር_ዳር #መስከረም_15_2019_ዓ_ም
✍️ በስማቸው አጥናፍ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
