ሰላምን አጥብቃችሁ ያዟት !

8

 

ሰላም በዋጋ የማይለካ እና ከምንም በላይ ቅድሚያ የሚሰጠው የሰው ልጅ የመኖር ሕልውና ነው። በአማራ ክልል ባለፉት ዓመታት በነበሩ ግጭቶች እና አለመረጋጋቶች የደረሱ ውድመቶች የሰላምን ዋጋ በግልጽ አሳይተዋል።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት ዋና ፀሐፊ መላዕከ ብርሃን ፍስሐ ጥላሁን ሰላም ሲታጣም ኾነ ሲደፍርስ የሚጎዱት የሰው ልጆች ብቻ ሳይኾኑ በምድር ላይ ያሉ ፍጥረታት ሁሉ ናቸው ብለዋል። ይሁንና ሰላም የሚታጣውም ኾነ የሚገኘው በሰው ልጆች ነው ይላሉ።

​የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አስተምህሮ በዋናነት ስለ ሰላም፣ ፍቅር እና የሕዝቦች ደኅንነት የሚሰበክበት እንደኾነም ገልጸዋል። ቤተክርስቲያኗ ለሕዝብ እና ለሀገር ሰላም ዘወትር የምትጸልይ ናት፤ አገልግሎቷም ሙሉ በሙሉ ለዚህ ቅዱስ ዓላማ የቆመ ነው ብለዋል። “አባቶች አርዓያ ኾነን በማስተማር ለሰላም ምሳሌ መኾን ይገባናል “ነው ያሉት።

ማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ላይም ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል ብለዋል። ለሀገር እና ለሕዝብ የሚጠቅሙ መልዕክቶችን ማስተላለፍ እንጂ ሰላምን የሚረብሹ ነገሮችን ማስወገድ እንደሚገባ ነው ያስረዱት። ግጭት የሚያመጣው ሞትን እና ውድመትን መኾኑን ተገንዝቦ በጸሎት እና በትዕግስት ሰላምን አስጠብቆ ታሪክን እና ትውልድን ማስቀጠል ይገባል ብለዋል።

የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት የአደረጃጀት እና ማኅበራት ኀላፊ ሼህ ሙሐመድ ሁሴን በእስልምና እምነት አስተምህሮ ሰላም መሠረታዊ ነው ብለዋል። ከአላህ ስሞች አንዱ “ሰላም” መኾኑን ነው የተናገሩት።

“ሰላም የሁሉ ነገር ምንጭ ነው፤ ሰላም ከሌለ የተዘጋጀ ምግብን እንኳ መጉረስ አይቻልም” ያሉት ኀላፊው ጥላቻ እና ተቃውሞ ተገቢ እንዳልኾነ አጽንኦት ሰጥተዋል። በየቤተ እምነቱ ሰላምን መስበክ፣ እጅ ለእጅ መያያዝ፣ ለጋራ ሀገር እና ለሰላም መቆም እንደሚገባም አሳስበዋል።

​የሃይማኖት አባቶች የሰላም ስብከታቸውን አጠናክረው በመቀጠል የጋራ ሀገርን ማስቀጠል ይገባል ነው ያሉት። ለሃይማኖቱ የሚታዘዝ ማኅበረሰብ ሀገሩን እንደሚንከባከብ ገልጸዋል። “ተዋደን እና ተከባብረን የጋራ ሀገር መገንባት ይገባናል ነው ያሉት።

#አሚኮ #peace #ኢትዮጵያዊ 🇪🇹

#ባሕር_ዳር #መስከረም_15_2019_ዓ_ም

✍️ ዘጋቢ፡- ሥራው ድንቅ ደሳለኝ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleአስደናቂው ባሕላዊ ምግብ ”አብዚ”
Next articleበወገራ ወረዳ በጫካ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ታጣቂዎች የሰላም አማራጭን መቀበላቸውን ቀጥለዋል።